– ፓርኩ ውስጥ ገብተው ለማልማት 24 ባለሀብቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፡-በአምስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር እየተገነባ ያለውና ለአንድ ዓመት ያህል የዘገየው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ መጠናቀቁ ተገለጸ።ፓርኩ ውስጥ ገብተው ፋብሪካዎችን ለመትከልና ለመገንባት 24 ባለሀብቶች መመዝገባቸው ተመልክቷል።
የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ቱሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን እየተገነባ የሚገኘው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው ማዕራፍ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን ከተጠናቀቁት ስራዎች መካከልም የአስተዳደር፣ የመረጃ ማዕከል፣ ለባንኮችና ለካፍቴሪያ የሚያገለግሉ ህንጻዎችና ሦስት ለናሙና የተሰሩ የፋብሪካ ሼዶችን ይገኙበታል።
የተጠናቀቁት ሦስቱ የፋብሪካ ሼዶች መከራየታቸ ውና ለአስተዳደር፣ ለባንክና ለካፍቴሪያ አገልግሎት የሚውሉት አምስት ህንጻዎች ደግሞ ለኪራይ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።ሼዶቹን ውል ገብተው የተከራዩት ሁለቱ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሲሆኑ፤ አንዱ ደግሞ ሳውዲ ባለሀብት መሆኑን አቶ ከፍያለው አብራርተዋል።
ሁለቱ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የዘይትና አንዱ የሳውዲ ባለሀብት ደግሞ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በመጠቀም ጭማቂዎች የሚያመርት ፋብሪካዎችን የሚተክሉ መሆኑን አመልክተው፤ ኩባንያዎቹም የፋብሪካ ማሽኖችን ከውጭ ለማስገባት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ ዘጠኝ ዩኒየኖች ደግሞ ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተው በ600 ሚሊዮን ብር የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ሁለተኛና ሦስተኛ የግንባታ ምዕራፍ የሚባሉት የአስፓልት መንገዶች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ፣ የውሃ ጉድጓድ ቁፍሮ፣ የቆሻሻ ማጣሪያ፣ የውሃና የስልክ መስመሮች ያካተተ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተካሄዱ መሆኑን አመልክተው፤ አፈጻጸማቸው ሁለተኛውና ሦስተኛው ምዕራፍ ግንባታዎች በተለያየ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታዎች ጥቅል አፈጻጸማቸው 78 በመቶ ደርሰዋል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታውና የአስፓልት ግንባታው በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ወደ ኋላ መቅረታቸውን ገልጸው፤ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች የውጭ ምንዛሬው ተፈቅዶ የሚገቡ ከሆነ ግንባታዎቹ ከሁለት ወራት ጊዜ በላይ እንደማይፈጁ አመልክተዋል።
‹‹መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የውጭ ምንዛሬው ችግር ካልተቀረፈ ስድስትና ሰባት ወራት ወረፋ ጠብቀን አይደርሰንም።ወደ 2013 ዓ.ም ሊሻገር ይችላል የሚል ስጋት አለን።በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩት ሁለተኛና ሦስተኛ ምዕራፍ ግንባታዎች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ተጠናቀው ለባለሀብቶች ዝግጁ ይሆናሉ ብለን እየሰራን እንገኛለን›› ብለዋል።
በጥናቱ መሰረት ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በውስጡ ከ100 እስከ 150 ሼዶችን መገንባት የሚያስችል ስፋት አለው። የመግቢያ በሩን ለዓይን ሳቢ በሆነ መልኩና 40 ሄክታር መሬት ላይም አረንጓዴ ልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ መጠናቀቅ ለአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ለክልሉና ለአገሪቱ ጭምር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ አቶ ከፍያለው ጠቁመው፤ ገበሬው የሚያመርተው ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ስለሚያስችል የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፤የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ግብርናውን ያዘምናል ብለዋል።
የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በስሩ ለፓርኩ ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት እንደሚኖሩት ገልጸው፤ የሻሸመኔ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ግንባታ 98 በመቶ መድረሱንና ሦስቱ የምርት ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች ግንባታም እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ቢያዝም ከውጭ ለሚገቡት የግንባታ ጥሬ ዕቃዎች የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አዳጋች በመሆኑ ግንባታው ሊጓተት መቻሉን ገልጸዋል። የካቲት 2010 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ270 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2012
ጌትነት ምህረቴ