አዲስ አበባ፡- ‹‹የብልህ ጅምር›› የተሰኘውና ወጣት ጥንዶች ላይ ትኩረቱን ያደረገው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መርሐ ግብር ሮድ ማፕ ፎር ኢንቲግሬቲንግ ስማርት ስታርት ኢን ኢትዮጵያ /RISE/ በሚል ስያሜ ወደ ሌሎች ክልሎችም ሊስፋፋ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የማስፋፊያ መርሐ ግብሩ ትናንት በስካይ ላይት ሆቴል ይፋ በተደረገበት ወቅት የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የብልህ መርሐ ግብር ከዚህ ቀደም ያለዕድሜ ጋብቻን ከመከላከል ባሻገር ያለዕድሜያቸው ያገቡ ሴቶች ወሊድን በእቅድ በመተግበር በጤናቸው፣ በትምህርታቸውና በኢኮኖሚያቸው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ በጤና ሚኒስቴር ትብብርና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እ.ኤ.አ ከ2016 አስከ 2019 ሲተገበር ቆይቷል።
መርሐ ግብሩ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በሚገኙ 36 ወረዳዎች ላይ ሲተገበር መቆየቱንም ሚኒስትር ዲኤታዋ አስታውሰው፤ ከ 63 ሺ በላይ ላገቡ ወጣት ሴቶች ተደራሽ በማድረግ ከእነዚህ ውስጥ ከ30 ሺ 500 በላይ የሚሆኑትን ወጣት ባለትዳሮች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ይህንንም መልካም ተሞክሮ በማስፋት በቀጣይ መርሐ ግብሩን በመደበኛ የጤና አገልግሎት ውስጥ በማካተት ሮድ ማፕ ፎር ኢንቲግሬቲንግ ስማርት ስታርት ኢን ኢትዮጵያ /RISE/ በሚል ስያሜ የሶማሌና አፋር አርብቶ አደር ክልሎችን በማካተት በስድስት የሀገሪቱ ክልሎች በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት እንደሚተገበር ጠቁመዋል።
መርሐ ግብሩንም ለማስፈፀምም ፖፕሊሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ(Population Service International Ethiopia)የቴክኒክ እንዲሁም ችልድረንስ ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዲሽን (Children’s Investment Fund Foundation) የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ሚኒስትር ዲኤታዋ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም መርሐ ግብሩ በማሳደግ በአምስት ዓመታት የትግበራ ቆይታ አንድ ሚሊዮን ወጣት ባለትዳሮችን ለማዳረስና ከእነዚህ ውስጥ ወደ 500 ሺ የሚሆኑትን በፍላጎታቸውና በምርጫቸው የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመደገፍ እቅድ እንዳለም ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ሽፋን 36 ነጥብ 5 ብቻ መሆኑን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ወጣት ጥንዶችን ኢላማ ያደረገው ይህ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት መርሐ ግብር በሁሉም ክልሎች እንዲስፋፋ ከተደረገና አገራዊ ከሆነ የአገልግሎት ሽፋኑን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2012
አስናቀ ፀጋዬ