ወራቤ፡- ‹‹ልጆቻችንን እስክርቢቶና እርሳስ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ቁርአን እንጂ የጦር መሳሪያ አናሸክማቸውም›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በስፍራው እንደደረሱም የስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአቀባበሉ በኋላ በከተማዋ ስቴድየም ለተሰበሰቡት የዞኑና የከተማዋ ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንዳመለከቱት፣ ኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና አብሮነት መጠበቅ ያስፈልጋል ነገር ግን በአንድነትና በሰላም ስም ታዳጊዎችን የጦር መሳሪያ ማሸከምና ስለጦርነት ማስተማር ተገቢ እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
‹በብሄርና በሃይማኖት የሚከፋፍሉንን በማረም፣በማስተማርና በመደመር መንገድ መጓዝ አለብን፣ ባለፉት 27 ዓመታት መስመር ብለን ነበር። መስመር ጠበበና ጉዞአችንን ስላስጨነቀው መደመርን አማራጭ መንገድ አድርገን መረጥን። የመደመር መንገድ ሰፊ ነው ያቻችላል፤ ይሸከማል። ብዙዎችንም አቅፎ ይይዛል። መስመር ግን በጥቂቶች ጥፋት ይበጠሳል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስመር በመደመር መንገድ መተካቱንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ መመራትና መጓዝ ያለባት በልጆችዋ እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በልጆችዋ ላብና ጭንቅላት በመደመር መንገድ እንደሚገባ ተናግረዋል። ‹‹የስልጤ ህዝብም ይህንን እንደሚያምንና መደመር መንገዳችን፣ ብልጽግና መዳረሻችን ነው ሲል አረጋግጧል›› ብለዋል::
አክለውም በተገኘው አጋጣሚና ጊዜ ሁሉ ከወገን ጋር ተገናኝቶ መጠያየቅ፣ ተቀራርቦ መነጋገር ሀገራዊ ህብረትንና አንድነትን ለማጠናከር ብሎም ለማጽናት ጠቃሚ እንደሆነ አመልክተዋል። በዚህ ልክ መጓዝ የደረቀ ፍቅርንና ቀልብን፣በማለዘብና ዝምድናን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
‹በወራቤ ከተማ ዛሬ የተገኘው ከስልጤና ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ተገናኝተን የደረቀ ፍቅርና ቀልብ ካለ ፈጣሪ የሚለመንበት በማድረግ አንድነታችንን ለማጠናከር ነው› ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጤ
ህዝብ በፍጹም ሰላማዊነቱና በታታሪ ሰራተኛነቱም እንደሚታወቅ ጠቅሰዋል። ህዝቡ ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ጥላቻ፣ መከፋፈል ግንባር ቀደም ጠላቱ እንደሆነ በመገንዘብ፣ችግሩን ለማስወገድ እንዲነሳ ጠይቀዋል።
‹‹በስልጤ ‹እዳ ያለበት እንቅልፍ አይወስደውም› የሚል አባባል መኖሩን በማመልከትም ዕዳ ያለበት ሀገር ስለተረከብን ሀገራችን በብልጽግና ማማ ላይ እስክትወጣ እኛ በስልጤ ባህል መሰረት ድህነትን በማሸነፍ የትውልድ ዕዳን እንከፍላለን›› ብለዋል። ስለዕዳ በማውራት ብቻ ሳይሆን በርትቶ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012
ዳንኤል ዘነበ