የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀንን አስመልክተን አሁን ‹እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት› ተብሎ የሚጠራው የቀድሞ ‹የካቲት 12 መሰናዶ› ትምህርት ቤት ጎራ አልን።
ትምህርት ቤቱን እንደቃኘነው ከአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞ የአጼ ኃይለሥላሴ ቤተመንግሥት ጀርባ መገኘቱ፣ የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ባለበት አካባቢ አቅራቢያ መሆኑ ታሪካዊነቱን ያጎላዋል። ትምህርት ቤቱ ሰፊ በሆነ ቦታ፤ ለየት ባለ ሁኔታ መገንባቱም ትኩረትን ይስባል።
ታሪካዊነቱ ጎልቶ በሚታይበት ይህ ትምህርት ቤት ውስጥ በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎች የዛሬውን የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን እንደማይዘነጉትና ስለ ታሪኩም ግንዛቤ እንደሚኖራቸው በመገመት ወደ ትምህርት ቤቱ ተገኝተናል።
ባላት ከፍተኛ የትምህርት ውጤትና ተጨማሪ ትምህርት ቤቱ ያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና አልፋ የትምህርት ዕድሉን ማግኘቷን የነገረችን ተማሪ ገበያነሽ ስመኘው በመጠኑም ቢሆን ስለሰማዕታት ሐውልት ግንዛቤው እንዳላት ከምላሽዋ ለመረዳት ችያለሁ።
ጊዜውን በትክክል እንደማታውቅና ነገር ግን ከ30ሺ በላይ ዜጎች በፋሽስት ጣሊያን በግፍ ተጨፍጭፈው እንደሞቱ፣ መታሰቢያ ሐውልትም እንደቆመላቸውና በየዓመቱ የካቲት 12 ቀኑ ታስቦ እንደሚውል አጫውታኛለች። ሐውልቱን በርቀት ከማየት ባለፈም እንዳልጎበኘችና በመታሰቢያ ቀኑም ተገኝታ እንደማታውቅም ተናግራለች።
አልፎ አልፎ ከሰዎች ከምትሰማውና ከታሪክ መጽሐፍት ከምታነበው በስተቀረ ሰፊ ግንዛቤ እንደሌላት ግን አልሸሸገችም። እርሷን ጨምሮ ብዙ ሰው ስለሀገሩ ታሪክ ለማወቅ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው ብላ አታምንም። ተማሪ ገበያነሽ በሁሉም የትምህርት አይነት ውጤቷ መካከለኛ እንደሆነና በጣም የምትወደው የትምህርት አይነትም ሥነ- ህይወት (ባዮሎጂ) እንደሆነ ገልጻልናለች።
ሌላዋ ያነጋገርናት ተማሪ ቤተልሄም ጥላሁን ናት። የሰማዕታት ሐውልት ለሀገራቸው መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች መታሰቢያነት እንደሆነ ነው ግምቷን የነገረችን። የምትማርበት ትምህርት ቤት የቀድሞ ስያሜውም ይሁን የአሁኑ ለምን እንደተሰጠውና ታሪካዊ ተያያዥነት እንዳለውም ለማወቅ አልሞከረችም።
ሲነገርም አለመስማቷን ነው ያጫወተችኝ። በታሪክ ትምህርትም ላይ እንዳላገኘችውና ከመምህሯም እንዳልሰማች ትናግራለች። ለታሪክ ትኩረት ሰጥታ እንደማታውቅና ከዚህ በኋላ ግን ግንዛቤዋን ለማሳደግ ጥረት እንደምታደርግ አጫውታኛለች።
ሌላዋ ተማሪ ሰላማዊት አዲስ ትባላለች። ወሩንም ቀኑንም ለማስታወስ አልቻለችም። ቀኑን አስታውሰናት ‹አርበኞች ድል ያደረጉበት ቀን ይሆን?› ስትል እርግጠኛ ያልሆነ ነበር ምላሿ። ታሪክ እንደሚማሩ ግን ነግራናለች።
የትምህርት ቤቱ የአካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ተከስተ ሐጎስ ተማሪዎቻቸውን ሲቀበሉ ትምህርት ቤቱ አሁን በሚጠራበት ስሙ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ስለሰማዕታት መታሰቢያ ግንዛቤ መፍጠሩ ተዘንግቶ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
ያለፈው ታሪክ ለዛሬ ማንነት መሰረት እንዳለው ስለሚያምኑ ለተማሪዎቻቸው ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ መስራት እንዳለባቸውና ከዚህ በኋላም የቤት ሥራቸው አድርገው እንደሚወስዱት ተናግረዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ማህበራቸው በየዓመቱ በመታሰቢያ ሐውልቱ ላይ የአበባ ጉን ጉን ከማኖር ባለፈ ታሪኩ እንዳይዘነጋ በግል፣በመንግሥት ትምህርት ቤቶችና በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በተለይም ወጣቱ ጀግኖች አባቶችና እናቶች የሀገራቸውን ዳር ድንበር በማስከበር የሰሩትን ታሪክ፣ እነርሱም ከጀግኖቹ ተምረው በየተሰማሩበት ጀግና እንዲሆኑ ግንዛቤ በመፍጠር ማህበሩ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ይገልጻሉ። ሁሉንም በማዳረስ ግን የበለጠ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ በመንበረጸባዎት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን የፀሎት ሥነ ሥርዓትና በተለያዩ ዝግጅቶች ዕለቱን ለማሰብ የሚደረጉ ሥነ ሥርዓቶች አንዳንዴ መቆራረጥ ይገጥማቸዋል።
በተለይም ቤተክርስቲያኗ ከሁለት ዓመት በፊት የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ባለመወጣትዋ ለፓትርያርክ ጽህፈት ቤት በማመልከት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል። እንዲህ ያሉ የትኩረት ማነሶች በዓሉ እንዲደበዝዝ ያደርጋሉ ብለዋል።
‹የካቲት 12 ቀን ፋሽስት ጣሊያን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሕፃናትና አቅመደካሞች ሳይቀሩ ቁጥሩ ከ30ሺ የሚልቅ ህዝብን አንገቱን በስለት እየቀላ ደሙ እንደጎርፍ እንዲወርድ በማድረግ፣በደብረሊባኖስም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መነኮሳትን በግፍ በመግደል በኢትዮጵያውያን ላይ የማይረሳ በደል ያደረሰ በመሆኑ ነው በየዓመቱ የምንዘክረው› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ በቀላሉ የሚታለፍ እንዳልሆነ ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባ አስምረውበታል። የሀገር መሪዎች ሲለዋወጡ ታሪኩም እንደሁኔታው እንደሚቀዘቅዝና ማህበሩ ግን አቅሙ በሚችለውና በሚያገኘው ድጋፍ ልክ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል።
የዛሬውን የመታሰቢያ ቀንም ከውጭም ከሀገር ውስጥም የተለያዩ እንግዶችን በመጋበዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ታሪኩ እንዲታወቅ በማድረግ በዘለቄታው ላይ መሰረት የሚሆኑ መልዕክቶች እንዲኖሩት በማህበሩ በኩል ጥረት ተደርጓል። በአድዋ ላይ ድል የተደረገው ፋሽስት ጣሊያን ቂሙን ሳይረሳ በኢትዮጵያውያን ላይ በጠራራ ፀሐይ የፈፀመው ግፍ ታሪክ በቀላሉ የማይዘነጋው በመሆኑ ነው በየዓመቱ የሚታሰበው። ዘንድሮም ለ83ኛ ጊዜ ታስቦ ይውላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012
ለምለም መንግሥቱ