. 54 ነጥብ 528 ቢሊየን ብር ፈሰስ ተደርጓል
. 39 ነጥብ 258 ቢሊየን ብር ቃል ተገብቷል
. የብድር ጫና ከከፍተኛ ስጋት ወደ መካከለኛ ስጋት ወርዷል
አዲስ አበባ፡- በ2012 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ከበይነ መንግሥታዊ ተቋማትና ከመንግሥታት ትብብር 54 ነጥብ 528 ቢሊዮን ብር ፈሰስ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 39 ነጥብ 258 ቢሊየን ብር ቃል መገባቱንም ሚኒስቴሩ ጠቁሟል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኢንፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ የስድስት ወራት የብድር ፍሰትና ግኝት ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ 54 ነጥብ 528 ቢሊየን ብር በገንዘብ፣ በአይነትና በቴክኒክ መልክ የተገኘ ነው፡፡ ገንዘቡ በክልሎች ለተለያዩ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ እየዋለ ነው፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው ገንዘብ ውስጥ 18 ነጥብ 237 ቢሊየን ብር ከበይነ መንግሥታዊ ተቋማት በብድር የተገኘ ሲሆን በ11 ነጥብ 23 ቢሊየን ብር ደግሞ በእርዳታ መገኘቱን ያብራሩት አቶ ሀጂ፤ ከተለያዩ ሀገራት መንግሥታት በብድር 10 ነጥብ 532 ቢሊየን ብር እንዲሁም 14 ነጥብ 736 ቢሊየን ብር በእርዳታ የተገኘ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ሀጂ ማብራሪያ ቃል የተገባው 39 ነጥብ 258 ቢሊየን ብር የታቀዱ ሥራዎችን ለማስፈጸም ከ3 እስከ 10 ባሉ ዓመታት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ነው። ይህ ገንዘብ የፕሮጀክቶች ሁኔታ እየታየ በየጊዜው የሚለቀቅ ሲሆን፤ ቃል ከተገባው ውስጥ 16 ነጥብ 38 ቢሊየን ብር በበይነ መንግሥታዊ ተቋማት በብድርና በእርዳታ መልክ የሚሰጥ ነው። 23 ነጥብ 22 ቢሊየን ብር የተለያዩ ሀገራት በብድርና በእርዳታ መልክ ለመስጠት ቃል የገቡት ነው።
ብድርና እርዳታ ካበረከቱትና ቃል ከገቡት በይነ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ የግብርና ልማት ፈንድ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አቶ ሀጂ አክለው እንደገለጹት ፤ ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በጋራ የብድር ትንተና ተከናውኖ ነበር። በተደረገው ትንተና በ2010 ዓ.ም ላይ ሀገሪቱ የብድር ጫና ከፍተኛ ስጋት ደረጃ ላይ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከከፍተኛ ስጋት ወደ መካከለኛ ስጋት መውረዷን ተናግረዋል። የዚህ መሻሻል ዋናው ምክንያትም የቻይና የንግድ አበዳሪዎች የዕዳ ክፍያ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ዋነኛው ምክንያት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012
መላኩ ኤሮሴ