አዲስ አበባ፡- በሜድሮክ እህት ኩባንያ ‹‹ሆራይዘን ፕላንቴሽን›› እየተገነባ ያለው የሸገር ዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ተጠናቆ ሥራ ሊጀምር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ::
በሆራይዘን ፕላንቴሽን የእቅድ ቢዝነስ ልማትና ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ይበልጣል ሽመልስ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ግንባታው ከተጀመረ ወራትን ያስቆጠረው የሸገር ዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ሥራው በጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተመራ እንደነበር የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በቀን 18 ሰዓት በመስራት ግንባታውን ማፋጠን እንደተቻለና ጎን ለጎንም የማሽነሪዎችንና የሌሎች ግብዓቶችን ግዢ ተፈፅሞ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል። የፋብሪካው የውስጥ ለውስጥ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ እየተሰራ እንዳለና በቀጣይ ሳምንታትም የማሽን ተከላው ስራ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
የማሽን ተከላውን የሚያከናውኑት የማሽን አቅራቢው ሙያተኞች ቢሆኑም ኢትዮጵያዊያን ኢንዱስትሪያልና መካኒካል ኢንጂነሮች በመሳተፍ ቀጣይ ፋብሪካውን ተረክበው የሚመሩበትን ልምድ እንደሚያካብቱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።
ቀደም ሲል ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ የስንዴ ግዢ ለመፈጸም እንዳልተቻለ ያስታወሱት አቶ ይበልጣል የሚመለከታቸው አካላት ባደረጉት ቀና ትብብር ለጊዜው ለሶስት ወራት የሚበቃ የስንዴ ግዢ መፈጸሙንም ገልጸዋል።
‹‹በሰዓት 80ሺ ዳቦ የሚያመርተው ይህ ፋብሪካ የተገነባው ከውጭ የሚመጣ ስንዴን በመተማመን አይደለም›› ያሉት ስራ አስኪያጁ ድርጅቱ ወደ ፊት በሰፋፊ መሬቶች ላይ ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆን ስንዴ የማምረት ዕቅድ እንዳለውና ለዚህም የሚረዳ ጥናት ማድረጉን አስረድተዋል።
በፋብሪካው የሚሰሩ ሰራተኞች እንደየወቅቱ የስራ ሁኔታ ቁጥራቸው የሚለያይ ሲሆን አሁን ላይ አንድ ሺ 500 የሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል። ፋብሪካው በቀጣይ በሙሉ አቅሙ ወደ ታለመለት ስራ ሲገባም ከስንዴ ማምረት እስከ ዳቦ ማከፋፈል ባለው የስራ ሰንሰለት ውስጥ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በቀን ሁለት ሺህ ኩንታል ስንዴ ፍጆታ የሚጠቀምና በሰዓት ሰማኒያ ሺ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን ፋብሪካው በአጠቃላይ 12 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ የመያዝ አቅም ያላቸው ሶስት ትልልቅ የስንዴ ጎተራዎች፣ የዱቄት ፋብሪካና በሰከንድ 18 ሊትር ውሀ ማመንጨት የሚችል የራሱ የጉድጓድ ውሃ ያለው ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ማምረት ስራው ይገባል ተብሏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012
ኢያሱ መሰለ