አዲስ አበባ፡- በመስኖ ልማት ዘርፍ በአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በቆላማ አካባቢዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የፌዴራል መስኖ ልማት ኮሚሽን አስታወቁ።
የመስኖ ልማት ኮሚሽነሩ ዶክተር ሚካኤል መሐሪ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት የመስኖ ዘርፉን ካሉበት ችግሮች ለማውጣት በሚያስችል መልኩ እንደ አዲስ የማደራጀት ሥራ ተሰርቷል። የአምስት አመትና የአስር አመት ስትራቴጂክ ዕቅድም ተነድፏል።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ ተቋሙ የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ ህዝብ በብዛት ባልሰፈረባቸው ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም በቀላሉ ሊለሙ የሚችሉና ከፍተኛ የከርሰምድር ውሃ ሀብት ያላቸው ቦታዎችን የመለየት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የሚታቀዱ ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው ጀምሮ ለማጠናቀቅ የተለያዩ ፈተናዎች ያጋጥሙ እንደነበር የሚገልጹት ኮሚሽነሩ፣ የካሳ ክፍያ ጉዳይ ለፕሮጀክቶች መጓተት ከፍተኛ ማነቆ እንደነበር አስታውሰዋል።
ማነቆዎች ሲፈቱ ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንደሚጠናቀቁ፣ የሥራ ቅልጥፍናም እንደሚጨምር የሰው ኃይልና በጀትም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማገዝ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ የከርሰምድር ውሃ ሀብት ባላቸው ሱማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ በመስኖ ለማልማት በፕሮጀክት ደረጃ መለየቱንና ለሚቀጥሉት አምስት አመታት የመስኖ ልማት ጥሩ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012
ለምለም መንግሥቱ