አዲስ አበባ፡- የመንግሥት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ካላቸው ብዛት አንጻር ሁሉንም ለመቆጣጠርና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የአቅም ውስንነት እንዳለበት የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ገለፀ።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሁን ባለው ወቅታዊ መረጃ 247 ሲሆኑ፤ የመንግሥት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ 50 ደርሰዋል። እነዚህን ተቋማት ኤጀንሲው የሚቆጣጠርበት አቅም፣ የሰው ኃይልና አደረጃጀት የለውም።
በግሉ የትምህርት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች እንደየ ፕሮግራማቸው ዕውቅና ለመስጠት ኤጀንሲው ዶክተሮችን፣ መሃንዲሶችንና የመሳሰሉት የሙያ ዘርፎች ላይ ቀጥሮ ማሰራት የሚችልበት አቅም አልፈጠረም የሚሉት አቶ ታምራት፤ ችግሩን ለመቅረፍ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ መምህራን የተቀመጡ መስፈርቶችን በመገምገም ለኤጀንሲው ተጨማሪ ጉልበት በመሆን የትምህርት ጥራትና አግባብነትን በጋራ ማረጋገጥ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ፤ የትምህርት ጥራት በአንድ ኤጀንሲ ቁጥጥርና ክትትል ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም። ጥራትና አግባብነቱ ከተጓደለ ከፍተኛ የሆነ የሀገር ውድቀት ስለሚያስከትል በተለይ የዩኒቨርሲቲ አመራርና መምህራን ብቁ ዜጋ በማፍራት ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።
የትምህርት ጥራት ሲታሰብ ቅድሚያ የሚመጣው መምህር ነው ያሉት አቶ ታምራት፤ መምህር በየጊዜው ራሱን እያበቃ የሚሄድ መሆን እንደሚገባውና ሁልጊዜም በዕውቀት፣ በአመለካከት፣ በስነ ምግባር፣ በመትጋት ለሙያው ተገዥ ሆኖ በታማኝነት ማገልገል መቻል ይጠበቅበታል ብለዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፤ የትምህርት ጥራቱን እየተፈታተኑት ያሉት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቋሚ መምህር ሆነው እያለ ከሲቪል ሰርቪስ መመሪያ ውጭ ሲቪያቸውን ብቻ በመሸጥ ከአራት በላይ ተቋማት ውስጥ ቋሚ ሰራተኛ ሆነው የሚያገለግሉ ግለሰቦች ናቸው። ይህ ደግሞ የትምህርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ሀገር የምትፈልገውን ብቁና የተማረ የሰው ኃይል እንዳታገኝ እያደረጋት ነው። መምህራን ይህን በመገንዘብ ለሙያቸውና ለህሊናቸው ተገዥ በመሆን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012
ሞገስ ተስፋ