አዲስ አበባ፡- ‹‹ሁሉም ሰው በራስ መተማመኑን አጎልብቶ ለእውነተኛ ውይይት ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል›› ሲሉ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
‹‹ችግሮቻችንን በውይይት መፍታት ለምን አቃተን›› በሚል ምክረ ሐሳብ ትናንት በሂልተን ሆቴል በአዕላፍ መልቲ ሚዲያ አዘጋጅነት በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ የውይይት መነሻ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡
እነዚህም ‹‹የውይይት አስፈላጊነት›› በቄስ ዶክተር ገለታ ሲጫሶ፣ ‹‹ውይይት ለአገር ግንባታ ያለው ፋይዳ›› በፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዲሁም ‹‹የውይይት ባህል እንዴት ገኖ ይውጣ›› የሚለው ደግሞ በፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንደተናገሩት፤ውይይት ከሰከነ መግባባትና መደማመጥ ጀምሮ እስከ ክርክር ድረስ ያሉትን ብዙ ነገሮች ይይዛል፡፡ የመጨረሻ ግቡ ይህ ነው ተብሎ የሚፈረጅ ሳይሆን በሂደት የሚከሰት ነው፡፡ ስለዚህም ሁሉም ሰው በራስ መተማመኑን አጎልብቶ ለእውነተኛ ውይይት ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ውይይት ሐሳብ ማመላለስ ውስጡ ያለበት ቢሆንም፣ ሀሳብ ማስተላለፍ ብቻም አይደለም፡፡ የውይይት ግብ ክርክር አሊያም ማሳመንም አይደለም፡፡ የተነሳበትን ግብ ሌሎች አምነው እንዲቀበሉ ጫና ማሳደርም አይደለም::
ውይይት ቀጥተኛ የሆነ የሐሳብ ማንሸራሸሪያ ሂደትም አይደለም፡፡በመሆኑም ውይይት የመጨረሻ ግቡ ይህ ነው የሚባል ሳይሆን ሁሌ የሚያድግና ሂደት ነው፡፡ የእውነተኛ ውይይት ባህሪ የሆነው በሂደት የሚከሰት መሆኑ፣ ሁሌም ደግሞ ወደየትም አቅጣጫ ሊሄድ የሚችል ሐሳብ አለበት፡፡ ሁሌም ሊገነባና ሊፈርስ እንደገናም ሊገነባ ይችላል፡፡ውይይት ሁሌም በፖለቲካ፣ በታሪክና ማህበራዊ አውድ ውስጥ ይፈጸማል፡፡
‹‹ለእውነተኛ ውይይት እንቅፋት ከሚሆኑት መካከል የኃይል ሚዛን ልዩነት አንዱ ነው፤ሌላው ደግሞ ሁሉም ሰው ወደ እውነተኛ ውይይት መግባት አለመፈለጉ ነው፡፡›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሁሉም ሰው በራስ መተማመኑን ሊያጎለብትና ለእውነተኛ ውይይት ራሱን ሊያዘጋጅ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
የአዕላፍ መልቲ ሚዲያ መስራችና ዳይሬክተር መጋቤ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው፤በአገሪቱ ያሉ ችግሮች በውይይት ይፈታሉ የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ለዚህም በሚል መድረኩን ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከእጅ ያልወጣ ነገር ግን ሊወጣ ጫፍ የደረሰ ችግር መኖሩን ባደረጉት መለስተኛ ጥናት መመልከታቸውን አስታውሰው፤እንዲህ አይነት የምክክር ጉባኤዎች በማካሄድና አንዱ ከሌላው ጋር እንዲቀራረብ በማድረግ ችግሮቹ ሊፈቱ የሚችሉ ስለመሆናቸው በምክረ ሐሳቡ ላይ ሐሳብ እንዲሰጥበት እንደሚፈልጉ አመልክተዋል፡፡
ምክረ ሐሳብ የሚሰጡት የኢትዮጵያ ህዝቦች መሆናቸውን ጠቅሰው፣እያንዳንዱ የራሱን ድርሻ እንደሚቀበልም ተናግረዋል፡፡ፖለቲከኞች የኢትዮጵያን አኩሪ እሴት ጠብቀው ፖለቲካቸውን እንዲያራምዱ ለማገዝና ለመደገፍ ይህ መነሻ ሐሳብ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
መጋቢ ዘሪሁን እንደገለፁት፤የምክረ ሐሳቡ ዋና ዓላማ እንደ አገር ያሉትን እሴቶች በማጉላት የሚነሱ ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህልን ማጎልበት ነው፡፡ የአገር ሰላምና የልማት አጀንዳን ከጥቂት ሰዎች ብቸኛ የባለቤትነት እጅ በማውጣት የህዝብ አጀንዳ ማድረግም ነው፡፡
ይህቺን አገር ወደፈለጉበት አቅጣጫ የመውሰድና የመመለስ መብት የተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዳይሆንና የኢትዮጵያ ህዝብ እየመከረ መልካም የሆነውን እንዲያቀርብም በመፈለጉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር ኢድሪስ፣መመካከርና መወያየት የሚጠቅመው ለማያውቅ ሰውና የተሳሳተን ለማቃናት መሆኑን ጠቅሰው፣አውቆ የጠመመን ግን ውይይትና ማስተ ማር እንደማያቃናው ተናግረዋል፡፡ በገንዘብ ውዴታ የተመረዘንና በስልጣን የተጠማን አካል ውይይት እንደማያቀናውም አስታውቀው፣ የሚያቀናው ጠበቅ ያለ መመሪያ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው፤ ‹‹ትልቁ ችግራችን መናናቅ ነውና ይህን ማስቀረት አለብን፡፡››ሲሉ ገልጸዋል፡፡መከባበርና መደማመጥ መሰረታዊ መሆናቸውንና ውጤታማ ውይይት ለማከናወንም እንደሚያስፈልጉ አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና ሌሎችም አካላት የተገኙ ሲሆን፣ጥያቄዎችም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል::
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
አስቴር ኤልያስ