የወረዳው የጽዳት ስራ በተለያዩ ወገኖች ይከናወናል፡፡ በመንግስት ሰራተኞች፣በማህበር በተደራጁ ስራ እጦች እና በግል ድርጅቶች ቆሻሻ የማሰባሰብ፣የማጓጓዝና የማስወገድ ስራ ይካሄዳል፡፡በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ፡፡
የወረዳው የደረቅ ቆሻሻ ማሰባሰብና ማጓጓዝ ቡድን መሪ አቶ ምትኩ ሺበሺ እንደሚሉት፤ 57 ተቀጣሪ የመንግስት ሰራተኞች ከሌሊቱ 10 ሰአት አንስቶ በፈረቃ የጽዳት ስራ ያካሂዳሉ፡፡በርካታ ስራ አጦችም በማኅበር ተደራጅተው በጽዳት ስራው ተሰማርተዋል፤ማህበራቱ በቅርቡም አንድ የሽርክና ማኅበር መሥርተው ቤት ለቤት ቆሻሻ መሰብሰብ ጀምረዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ጽህፈት ቤት የደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብ ፣ማጓጓዝና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ጥላሁን በዛብህ እንደሚሉት፤በክፍለ ከተማው ቆሻሻ በማንሳት ስራ የተደራጁ ሦስት ኢንተርፕራይዞች በአሥር ወረዳዎች ቤት ለቤት በመሄድ ደረቅ ቆሻሻ ይሰበስባሉ፡፡ከአንድ አባወራ በሳምንት ሁለት ቀን ቆሻሻ ይነሳል፡፡ኢንተርፕራይዞቹ ተራ ሲደርሳቸው ጠረጋም ያካሂዳሉ፡፡
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ ስራውን የጀመሩት ቆሻሻውን በጀርባቸው እየተሸከሙ ነበር፤ከዚያም ወደ በጋሪ፣ ከጋሪ ደግሞ በመኪና ቆሻሻውን በመሰብሰብ ወደ ማጓጓዣ ጣቢያ ይወስዳሉ፡፡ይህ ቆሻሻ በመንግሥት መኪና ወደ ረጲ ይወሰዳል፡፡ የሽርክና ማኅበራቱ ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶውን ይቆጥባሉ፡፡በቆጠቡት ገንዘብ በአሁኑ ወቅት 9 መኪናዎች ገዝተው እየሰሩ ናቸው፡፡
ሁለት የግል የጽዳት ድርጅቶችም የትላልቅ ተቋማትን ቆሻሻ በመሰብሰብ ወደ ማስወገጃ ሥፍራ ይወስዳሉ፡፡ የመንግሥት ተቀጣሪ የፅዳት ሠራተኞች ደግሞ በክፍለ ከተማው የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶችንና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እንደሚያጸዱ አቶ ጥላሁን ተናግረው፣አንደኛ ደረጃ መንገዶችን በማሽን ማጽዳት እንደተጀመረም ያመለክታሉ፡፡
‹‹ቆሻሻ ሀብትና ገንዘብ መሆኑ ታውቋል፤በኪሎ ይሸጣል፡፡በየቦታው መጣሉ እየቀረ ነው፡፡››ሲሉ ጠቅሰው፣ፕላስቲክ የውሃ ኮዳዎች እንደፊቱ አሁን በየቦታው እንደማይጣሉም ይገልጻሉ፡፡ሰዎች ጠጥተው ሳይጨርሱ ኮዳዎቹን ለመውሰድ የሚረባረቡበት ሁኔታ መፈጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡ቆሻሻ ሰብስበው በሚከፈላቸው ገንዘብ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ በርካታ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ጥላሁን፣‹‹በጽዳት አመርቂ ደረጃ ላይ ደርሰናል ባንልም የተሻለ ለውጥ አምጥተናል፡፡” ሲሉም ነው የሚናገሩት::
በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ያሉ በደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብ ላይ የገቡት የጎዳና ተዳዳሪዎችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደነበሩ አስታውሰው፣እነዚህ ወደ 37 በሚሆኑ መደበኛ ያልሆኑ ማኅበራት የተደራጁ ወገኖች ደረቅ ቆሻሻ በመሰብሰብ እና ወደ ማስወገጃ ቦታ በመኪና በመጫን እንደሚሰሩ ይገልጻሉ ፡፡እነዚህ 37 ማኅበራት ሦስት ሽርክናዎች እንዲመሰርቱ ተደርጓል ይላሉ፡፡
‹‹መንገዶቻችን ጸድተዋል፤ቆሻሻ እንደ ፊቱ በየቦታው ተዝረክርኮ አይታይም፤ ኅብረተሰቡ ቆሻሻውን በየቤቱ አከማችቶ ይጠብቃል ፤ከዚያም ለሰብሳቢዎች ያስረክባል›› የሚሉት አቶ ጥላሁን፣ይህም ከተማችን በደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ ላይ የነበራት መጥፎ ገፅታ መለወጡን ያመለክታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ የአገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ኃይሉ እንደሚሉት፤ በመዲናዋ በቆሻሻ መሰብሰብ፣ማጓጓዝና ማስወገድ ላይ 74 የሽርክና ማኅበራት ተሰማርተዋል፡ወደ 6ሺ የሚጠጉ አባላትም አሏቸው፡፡ 70 በመቶው ደረቅ ቆሻሻ ወደ ረጲ ኃይል ማመንጫ ገብቶ በየቀኑ 25 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ይመነጭበታል፡፡ለዳግም ዑደት የሚያገለግሉትና የሚቃጠሉት ከተለዩ በኋላም የማይቃጠለው ይቀበራል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤74ቱ የሽርክና ማኅበራት በፊት በጀርባ እየተሸከሙ ነበር ቆሻሻ እየሰበሰቡ የሚያጓጉዙት፡፡ኤጀንሲው ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት ከአዲስ ካፒታል ጋር በማገናኘት መኪኖች ከውጪ በማስመጣት እንዲገዙ እየተደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቆሻሻ ከቤት ለቤት የሚያወጡባቸው አይሱዚ መኪናዎች ባለቤት ሆነዋል::
በሽርክና ሥር ያለ እያንዳንዱ ማኅበር ቢያንስ ሁለት መኪና እንዲኖረው ታስቦ እነሱ ግን አሁን ወደ 160 መኪና ገዝተዋል፤ወደ 40 የግል የጽዳት ድርጅቶች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም ለጽዳት ሥራቸው የሚረዳቸው ወደ 105 መኪናዎች አሏቸው::
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መጀመሪያ ቤት ለቤት እየሄዱ ቆሻሻ ሲሰበስቡ በሳምንት ሳንቲም ይቀበሉ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ እነዚህ ማኅበራት ናቸው አቅም እየፈጠሩ መጥተው ሽርክና መመስረት ውስጥ የገቡት ይላሉ፡፡ሽርክናዎቹም ሌሎች የራሳቸውን ድርጅቶች ለመመሥረት እየሰሩ እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤በቆሻሻ መሰብሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ማስወገድ ላይ ሦስት ዓይነት ክፍያ አለ:: በሽርክና የሚሠሩት የመዲናዋን 80 በመቶ ቆሻሻ ይሰበስባሉ፡፡ ለእነዚህ ከፍተኛው ክፍያ ይፈጸማል፤ ከመንግስት ሰራተኛም የተሻለ ደሞዝ የሚያገኙ አሉ:: በግል እስከ 13ሺ ብር የሚያገኙ አሉ ፡፡ደከም ያለው ደግሞ እንደ ሥራው መጠን ከ7ሺ እስከ 8ሺ የሚያገኝም አለ፡፡የግሎቹ በሠሩት መጠን ድርጅታቸው ይከፍላቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ