አዳማ፡- በሱማሌ ክልል ባሉ በቃሎጂ አንድና ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ70 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወነ ያለው ሥራ በቂ አለመሆኑን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡ መረጃ የማይሰጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ተቋማት እየጨመሩ መምጣታቸውም ተጠቁሟል፡፡
ተቋሙ የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን ትናንት በአዳማ ከተማ በገመገመበት ወቅት የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ እንደገለፁት፣ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት ለማስፈፀም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ከወቅታዊ ተግባራት አንፃር ባለፉት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመንግሥት በኩል መልሶ ለማቋቋም የተሰራውን ሥራ ተከታትሏል፡፡
በዚህም በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልላዊ መንግሥታት የተሰራው መልሶ የማቋቋም ሥራ አመርቂ ሆኖ ማስተዋሉን የጠቆሙት ዶክተር እንዳለ፣በሱማሌ ክልል ባሉት ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች ቃሎጂ አንድና ሁለት ያሉ ከ70 ሺ በላይ ተፈናቃዮችን በተመለከተ እየተሰራ ያለው የማቋቋም ሥራ በቂ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች ለከፍተኛ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ችግር መጋለጣቸውንና ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያም መንግሥት በቂ ትኩረት እንዳልሰጠው ተቋማቸው ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
የመረጃ ነፃነትን ተፈጻሚ በማድረግ ረገድም ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ያመላከቱት ዋና እንባ ጠባቂው፣ዜጎች መረጃ የመጠየቅ፣ የመውሰድና የማስተ ላለፍ መብት ቢኖራቸውም፤ መረጃ የማይሰጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ተቋማት ከእለት ወደ እለት እየጨመሩ መጥተዋል ብለዋል፡፡ለዚህም የግንዛቤ ችግር ሳይሆን አዋጁ ውስጥ መረጃ የሚከለክል አካል ምን ይደረጋል የሚለው ላይ የተጠያቂነት ክፍተት መኖሩ አብይ ምክንያት ሆኖ እንደሚጠቀስ አመልክተው፣ይህም በህጉ ላይ በግልፅ መቀመጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የተቋሙ የበጀትና እቅድ ክትትል ዳይሬክተር አቶ አዱኛ ሙሉነህ በበኩላቸው፤የተቋሙ ሥራ በወቅቱ ሀገራዊ አንገብጋቢ ሁኔታ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታና ደረጃ እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ ምስል በዳታ በተደገፈ መረጃ ለምክር ቤቱና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ማቅረብ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንንም ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ከመሰል ጠንካራ ሥራዎች ባሻገር ያለፉትን ስድስት ወራት በተለይም በዋናው መስሪያ ቤት ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ያለመስጠት፣ በኦዲት ግኝት፣ የሀብት አጠቃቀም እንዲሁም ከተራድኦ የሚገኙ ገንዘቦች በአግባቡ መጠቀም አለመቻልም ዋና ዋና ውስንነቶች ሆነው መስተዋላቸውንም አቶ አዱኛ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
ታምራት ተስፋዬ