አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የሰው ሀይል ምርታማነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ተጠባባቂ ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ዮሀንስ አያሌው፣ በኢትዮጵያ የሰው ሀይል ምርታማነት ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ የጥናት ሪፖርት ትናንት ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ የሰው ሀብት ምርታማነት ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ቢሆንም፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሰው ሀይል ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የምርታማነት ደረጃ ዕድገት አምስት በመቶ መሆኑን ጥናቱ እንዳመላከተ አስታውቀዋል፡፡
በኢኮኖሚ ሴክተሩ ላይ ያለው የሰው ኃይል ምርታማነት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ጥናቱ አመላክቷል ያሉት ጄነራል ዳይሬክተሩ፣ግኝቱም በሰው ሀብት ልማት ላይ ለሚወጡ ፖሊሲዎች ግብዓት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ ለኢኮኖሚያዊ እድገት የሰው ሀይል ምርታማነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
‹‹የሰው ሀይል ምርታማነት ላይ የተመሰረት ፖሊሲ እንደ ሀገር ባለመኖሩ ምርታማነት እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡›› ሲሉ ገልፀው፤ የቀድሞ ፖሊሲዎች ኢንቨስትመንትን በመሳብ ላይ ያተኮሩና ለዘርፉ ትኩረት ያልሰጡ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው ሀገራዊ እድገት ዋንኛ ምንጭ የካፒታል ኢንቨስትመንት ነው፤ ይህም ብዛትን መሰረት አድርጎ ይሰራበት ስለነበር ጥራት ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖን ፈጥሯል፡፡ ያለውን ሀገራዊ ሀብት በተገቢው መልክ ለመጠቀም ጥራትን መሰረት በማድረግ መስራት ይገባል፤ይህን የሚመራ የሰለጠነ የሰው ሀብት ልማት አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡
የጥናቱ አስተባባሪ ዶክተር ኪዳነማርያም በርሄ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ ሀገሪቱ በሰው ሀይል ምርታማነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ ኢኮኖሚው ላይ የተሻለ ውጤት እንዳይመዘገብ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
‹‹ሀገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ በትንሽ የሰው ሀይል ብዛት ያለውና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡›› ያሉት የጥናቱ መሪ፣ የበለፀጉ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት መሰረቱ ምርታማ የሰው ሀይል ማፍራት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡
‹‹ምርታማነትን ለማሳደግ የሰው ሀብት ልማት ላይ ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት፤ሀገሪቱ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰራና በባለቤትነት የሚመራ ተቋም ያስፈልጋታል፡፡›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደና ሶስት ዓመታትን ወስዷል የተባለው ይህ ጥናት በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትና በጃፓን ናሽናል ኮፕሬሽን ኤጀንሲ ትብብር የተካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
ተገኝ ብሩ