አዲስ አበባ ፡-በቀጣዮቹ አስር አመታት 200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ግንባታ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ላይ እንደሚካሄድ የከተማዋ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂሬኛ ሂርጳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ፤የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እቅድ መነሻ በሆነው በዚህ የግንባታ ፕሮጀክት ኤጀንሲው በሙከራ ደረጃ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከለቡ ጀሞ ቁጥር አንድ የ2 ነጥብ 7 ኪሎሜትር የብስክሌት መስመር አስገንብቶ ወደ ስራ አስገብቷል፡፡200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ደግሞ በቀጣይ ይገነባል፡፡
ለግንባታው የአዋጪነት ጥናት ተካሂዶ ወደ ጨረታ ሂደት እየገባ ያለው የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ግንባታ ከሃያት መገናኛ ያለው መስመር መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ በዚህ አመት ተቋራጭ ገብቶበት ግንባታውን እንደሚያከናወን አስታውቀዋል፡፡
መስመሩ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ ከሃያት፣ ሰሚትና ሲ ኤም ሲ አካባቢዎች ለሚመጡ መንገደኞች አማራጭ የትራንስፖርት ዘዴ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ኤጀንሲው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጀሞ አካባቢ ከሚያከናውናቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ የብስክሌት ትራንስፖርት መስመሮቹ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ እየተሰራ ባለው አዲሱ የቃሊቲ መንገድም የብስክሌት መስመር ተካቶ እየተሰራ ነው:: በሂደትም የብስክሌት መስመሮቹን ውጤታማነት በመገምገም በሌሎች አካባቢዎች ላይ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎቱ እንዲስፋፋ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
አስናቀ ፀጋዬ