በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መደበኛ የጋዜጠኝነት ስራ ከሚሰሩት ሙያተኞች በተጨማሪ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅተው በማቅረብ፤ በማስተዋወቅ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ሙያተኞች ጋዜጠኛ ናቸው፤ ወይም አይደሉም በማለት መከራከሪያ ሀሳቦች ይቀርባሉ። በዚሁ ላይ የዘርፉ ምሁራንና ሙያተኞች የተለያዩ ሃሳቦች ይሰጣሉ።
በመገኛና ብዙሃኑ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠይቀውን ስነ ምግባር፣ እውቀትና ክህሎት መሰረት አድርገው ስራቸውን በአግባቡ የሚከውኑ ጋዜጠኞች የመኖራቸውን ያህል፤ ያለ በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ሙያዊ ስነ ምግባር በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የአየር ሰዓት በመውሰድ መርሀ ግብሮችን የሚያቀርቡ ግለሰቦች በሙያው እድገት ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙ ዩኒዩኬሽን ትምህርት መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ፤ ጋዜጠኝነት መረጃ መሰብሰብ ማደራጀትና በተለያዩ መንገዶች ማስተላለፍ የሚሉትን ፅንሰ ሃሳቦች በሥርዓት የሚመራበት ሙያ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ወቅቱ ያመጣውና ስለ ጋዜጠኝነት የሚሰጡ የተለያዩ ብያኔዎች በሙያው ላይ ወጥ የሆነ አቋምና ብያኔ እንዳይኖር አድርገዋል ይላሉ።
ይህን መሰረት በማድረግ “ጋዜጠኛ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ የጠራ ምላሽ ለማግኘት የሙያውን ዓላማ መግለፅና ከብያኔው ጋር ማጣጣም ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ። ጋዜጠኝነት ዓላማው የህዝብን ሰፊ ፍላጎት ማሟላት መሆኑን የሚገልፁት ዶክተር ሙላቱ፤ ለዚህ ዓላማ በመስራትና ባለመስራት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ለሙያው የቀረበውና ጋዜጠኛ ማን ነው? የሚለውን ምላሽ ለማግኘት እንደሚያስችል ያመለክታሉ።
እንደመምህሩ ገለፃ፤ አንድ ጋዜጠኛ ለሙያ የሚያበቁት ክህሎት፣ እውቀትና ሙያዊ ስነ ምግባር በተላበሰ መልኩ መረጃዎችን ሰብስቦና አጠናክሮ የሰፊውን ህብረተሰብ ፍላጎትና አላማ ለማሳካት የሚሰራ መሆን ይጠበቅበታል። ከዚህ በተለየ መልኩ በሚዲያዎች የሚታዩ የተለያዩ መርሀ ግብር የሚያስፈፅሙና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን አዘጋጅተው የሚመሩ ሁሉ ጋዜጠኛ ናቸው ማለት የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑን ያስረዳሉ። በዚህም ጋዜጠኝነት እየተሰጠው ያለ የተሳሳተ ብያኔ ሊጠራ እንደሚገባውም ያሳስባሉ።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ተግባር አክብረው የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ፤ ስራውን ሳያውቁና መርሆቹን ሳይከተሉ የሚሰሩ ግለሰቦችና አንዳንድ ሚዲያዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ። የጋዜጠኝነትን ሙያ በሶስት የሚከፍሉት ዶክተር ሙላቱ፤ የመጀመሪያዎቹ የሙያው ስነ ምግባርና እውቀት ሳይኖራቸው ወደ ሚዲያ ተቀላቅለው የራሳቸውን ወይም የሚዲያውን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ የሚጥሩ ሲሆኑ፤ የዚህ አይነት የጋዜጠኝነት ሙያ ከሙያው ስነ ምግባር ያፈነገጠና ዓላማውን የሳተ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሁለተኛው የጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሚገኙት የሙያውን ሥነ ምግባር ሆን ብለው የማይጥሱና ስራውን በትክክል ለመከወን የሚጥሩ የሰፊውን ህብረተሰብ ፍላጎትን ባማከለ መልኩ ስራቸውን የሚከውኑ ጋዜጠኞች ናቸው። እነዚህ ጋዜጠኞች የተሻሉ መሆናቸውና ሙያውን በመጠኑም ቢሆን የሚተገብሩ መሆኑን ገልፀው፤ እነሱም ላይ ሙያው የሚጠይቀውን እውቀት፣ ክህሎትና ሙያዊ ሥነ ምግባርን በመላበስ በኩል ውስንነት ይታይባቸዋል ብለዋል።
ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱንም ባህሪያት እያፈራረቁ እንደ ሚዲያው ባህሪይ ለዋውጠው ስራቸውን የሚያከና የሚያከናውኑ ሙያተኞች ደግሞ በባህሪያቸው የተለዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ ጋዜጠኞች አንዴ የራሳቸውንና የተቋማቸውን አሊያም የቡድናቸውን ፍላጎት ሲያንፀባርቁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማህበረሰቡን ፍላጎትና ዓላማ ለማሳካትም ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። እነዚህም ቢሆን የሙያውን ሥነ ምግባር ያሟሉ አይደሉም። እነዚህ ሙያውን አውቀው የማይተገብሩ ናቸው።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህሩ አቶ ፍሬዘር እጅጉ ጋዜጠኝነት በብያኔ ደረጃ አከራካሪ መሆኑን ያስረዳሉ። ጋዜጠኝነት ፍላጎት ያለውና ሊሰራው የሚፈልገው ሰው ሁሉ ሊሰራው የሚችል ሙያ አድርገው የሚወስዱት እንዳሉ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ሙያውን የሚሰራው የጋዜጠኝነት ሙያ ያለውና በሥነ ምግባር የሚመራ ሰው መሆኑን ይገልፃሉ። በሚዲያ ላይ የሚሰሩና የተለያዩ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅተው የሚያቀርቡ ሁሉ ጋዜጠኛ ሊባሉ እንደማይችሉ ያስረዳሉ።
መምህር ፍሬዘር የጋዜጠኝነት ሙያ እንደ ሀገር በአነስተኛ የሙያተኝነት ደረጃ ላይ ይገኛል በማለት ገልፀው፤ ለዚህም ምክንያቱን ሲያብራሩ በሙያው ላይ ያሉ ሰዎች መሰረታዊ የሆነ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠይቀውን ስነ ምግባር፣ እውቀትና ክህሎት ያልጨበጡ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ሙያው በሙያተኛ አለመመራቱ ለተለያዩ ችግሮች መንስዔ መሆኑን አውስተው፤ ሚዲያዎች የማህበረሰቡን ተአማኒነት እንዲያጡ እያደረጋቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
የድሬ ቲዩብ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ በበኩላቸው፤ ጋዜጠኝነት ሙያውን የሚወድና ሊሰራበት የሚፈልግ ሰው ሁሉ መርሁን ተከትሎ መስራት የሚችለው ሙያ መሆኑን ያስረዳሉ። ጋዜጠኛ ለመሆን የግድ የጋዜጠኝነት ትምህርት አስፈላጊ አይደለም የሚሉት ጋዜጠኛ ፍሬው፤ የሙያው ክህሎት ያለው ሰው ሊሰራው የሚችለው ነው በማለት ያስረዳሉ።
ከጋዜጠኝነት ሙያ ውጪ ያለ ሰው በጋዜጠኝነት መሳተፉ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ብዙም ሊሆን አይችልም የሚሉት ጋዜጠኛ ፍሬው፤ የተሳታፊው ፍላጎትና ክህሎት ግን ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ። የሙያው ሥነ ምግባር አክብረው የሚሰሩና ሙያውን የሚተገብሩ ሁሉ ጋዜጠኛ ናቸው በማለት አቋማቸውን ይገልፃሉ ።
በሚዲያ ላይ ያሉ ሙያተኞች የሥነ ምግባር፣ የክህሎትና የእውቀት ክፍተት የሚታይባቸው መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያዎቹ፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ ሙያተኞች እራሳቸውን ከሙያው ጋር በማላመድና የሙያውን ሥነ ምግባር በማክበር ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
ተገኝ ብሩ