በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ ብሔርን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርንና ፆታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ሆን ተብሎ የሚፈፀምን ጥቃት ለመከላከል፤ እንዲሁም የመረጃውን እውነተኛነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳይደረግ የሚሰራጭ ሁከትን ወይም ግጭትን የሚያነሳሳ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የሚያደርግ የሃሰት መረጃ ለመከላከል በሚል ባሳለፍነው ሳምንት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን የሚከለክል አዋጅ ፀድቋል።
አዋጁ ሰፊ ክርክር የተካሄደበት ሲሆን፤ ብዙዎች ወቅቱን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት የአዋጁን መውጣት ደግፈዋል። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ደግሞ የመናገር መብትን ይገድባል በሚል እና በሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች የአዋጁን መፅደቅ ተቃውመዋል። የአዋጁን መውጣት መቃወም ባይሆንም ቀድመው ስጋት እንዳለባቸው ሲገልፁ ከነበሩት መካከል የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ እንዱ ናቸው።
እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለፃ፤ አዋጁ የጥላቻ ንግግር መከላከል ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨትን የሚያጠቃልል ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የዚህ አይነት ህግ የወጣበት ምክንያት የሚያግባባ ቢሆንም፤ ከብዙ አገሮች ልምድ መመልከት እንደተቻለው በተለይ የተሳሳተ መረጃ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ብዙ ጊዜ የመገናኛ ብዙሃንን እንደማጥቂያ መሳሪያ ያገለግላል።
ህጉ አዲስ አለመሆኑን እና ከዚህ በፊትም በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ አዋጅ ሥራ ላይ ውሎ እንደነበር አስታውሰው፤ የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨትን የተመለከተው የአዋጁ ክፍል መካተት የለበትም ብለው እንደነበር አመልክተዋል።
የጥላቻ ንግግር ጉዳይ ግን በዓለም አቀፍ ህግም የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ መሰረት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ አገሮች እንዲህ አይነት ህግ እንዲያወጡ የሚጠበቅ መሆኑን እና በእርሳቸው በኩልም ይህንን የተመለከተው አዋጅ እንዲወጣ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
እንደኮሚሽነሩ ገለፃ፤ የጥላቻ ንግግር መከላከያ ህጎች አወጣጣቸው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በጣም በጠባቡ ካልተቀረፁ ተተርጉመው በተለያየ መልኩ ሥራ ላይ ከዋሉ በሌሎች የሰብአዊ መብቶች ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። ስለዚህ ቀድሞ ሲዘጋጅ ይህንኑ ሃሳብ አቅርበዋል። አሁን የፀደቀው አዋጅ ላይ ያቀረቡት ጉዳዮችም ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አግኝተው እነርሱ ባሉት መልኩ በጠባቡ ተዘጋጅቷል።
የተሳሳተ መረጃ ይዘት ግን ስጋት እንደፈጠረባቸው ጠቁመው፤ አስፈላጊነቱን የተረዱ በመሆኑ አለአግባብ ስራ ላይ መዋሉን አስመልክቶ በቅርብ ክትትል የሚያደርጉ መሆኑን ተናግረዋል። “ህጉ ሆን ተብሎ በመንግስት፣ በፖሊስም ሆነ በአቃቤ ህግ ነፃ ሃሳብን ለማፈኛነት መጠቀሚያ መሆን አለመሆኑን ስልታዊ ክትትል እናደርጋለን።” በማለት ተናግረው፤ መገናኛ ብዙሃንን እና ጋዜጠኞችን ያለአግባብ ለመክሰስ እንደመሳሪያነት ተጠቅመውበታል ወይስ አልተጠቀሙበትም የሚለውን ለመከታተል ብዙም የሚያስቸግር አለመሆኑን አብራርተዋል።
ጨምረውም ዋናው ጉዳይ ህግ በአወጣጡ ላይ ብቻ ሳይሆን በአተገባበሩ ላይም መሆኑ እና በአግባቡ ክትትል እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። ሌላኛው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህሩ አቶ በረከት ሃሰን፤ የጥላቻ ንግግር እና የተሳሳተ መረጃ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን እና እንድን ሰው ወይም ብሔር ወይም ሃይማኖት በመስደብና በመፈረጅ የሚፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታም ሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል በመሆኑ የአዋጁ አስፈላጊት አያጠያይቅም ብለዋል። ዋናው ጉዳይ በአዋጁ ውስጥ የተካተቱ ሃሳቦች በትክክል ለታለመላቸው ዓላማ ማዋል የሚችሉ ናቸው? ብሎ መመዘኑ የተሻለ መሆኑን አቶ በረከት አመልክተው፤ ብዙዎቹ አዋጁን የሚቃወሙት የመናገር መብትን ያፍናል ከሚል መነሻ መሆኑን ተናግረዋል።
“የሽብር አዋጁም ብዙ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። አዋጁ ውስጥ የተካተቱት ጉዳዮች ከማጨቃጨቃቸውም ባሻገር የሚመለከታቸውን ያህል ውይይት የተደረገባቸው አልነበሩም” ብለው፤ በመጨረሻም የግምገማው ውጤት አዋጁ ትክክል አይደለም በሚል ወደ መቀየርና እና ወደ ማሻሻል የተገባ መሆኑን አስታውሰዋል። እንደሽብር አዋጁ ሁሉ ይህ አዋጅም በቂ ውይይት ተደርጎበታል የሚል እምነት እንደሌላቸው፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ውይይት እንዳልተደገረበት ተናግረዋል።
በትክክል የሚመለከታቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ በጉዳዩ ላይ እውቀት ያላቸው የህግ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በበቂ መጠን የተሳተፉበት ነው ለማለት እንደሚቸገሩም ገልፀዋል። በጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ማርቀቅ እና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው፤ በ1997 የወጣው የወንጀል ህግ በመሰረታዊነት ዘመናዊ ወንጀሎችን፤ የሳይበር ጥቃትን ጨምሮ የህገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ሌሎች ብዙ ጉዳዮችን አሟልቶ ባለመገኘቱ በህጉ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት አዋጁ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በወንጀል ህጉ በአንድ ሰው ላይ የሚፈፀምን ስድብና ዛቻ በሚመለከት ተጠያቂ ለማድረግ በግልፅ ቢደነገግም፤ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ የሚፈፀም ስድብን አስመልክቶ ተጠያቂ የሚሆንበት የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ይህኛው አዋጅ ወጥቷል ብለዋል።
“ቀድሞ የሌሎች አገራት ተሞክሮ በማካተት ክልሎች ድረስ በመዝለቅ ዝርዝር ጥናት ተካሂዷል።” ካሉ በኋላ ምንም እንኳን በህገ መንግስቱ ሃሳብን የመግለፅ መብት የተቀመጠ ቢሆንም ገደብ የሚያስፈልገው በመሆኑ ጥናት ላይ በመመርኮዝ ለህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት ሲባል አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ለመከላከል ሲባል ገደብ መጣሉ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መፅደቁን ተናግረዋል።
በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ድረገፆች የሚሰራጩ አደገኛ ሃሳቦች መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ በላይሁን፤ እነዚህን በህግ ሥርዓት ማስያዝንም ማዕከል ተደርጎ አዋጁ መዘጋጀቱን አብራርተዋል። አዋጁ በረቂቅ ደረጃ እያለ በመገናኛ ብዙሃን ጥሪ በማድረግ ተደጋጋሚ ውይይት የተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግም ሆነ ፓርላማው ራሱ ከሚገባው በላይ ተደጋጋሚ ጥሪ በማቅረብ ውይይት የተካሄደበት መሆኑን ተናግረዋል። አዋጁን ወደ ፊት ለማስተግበር የሚያዳግት አለመሆኑንም አቶ በላይሁን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
ምህረት ሞገስ