ኢዜአ (ጅግጅጋ)፡- በመንግስት የተጀመሩ የብልጽግና ጉዞዎችን ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚ ወጡ በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የብልጽግና ጉዞን የሚደግፉ የተለያዩ መልዕክቶችን አሰምተዋል።
በጅግጅጋ ስታዲየም ‹‹በህብር ወደ ብልፅግና፣ ብልፅግና ለሁሉም፣ ሁሉም ለብልፅግና›› በሚል ትናንት የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል። በድጋፍ ሰልፉ ለውጡ የክልሉን ፍትሃዊ የስልጣን ባለቤትነትና አካታችነት ያረጋገጠ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተገኙት መካከል የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎችን በመወከል የተናገሩት ገራድ አብዲማሊክ እንዳሉት፤ የብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት የሚያሳትፍ ነው። የብልፅግና ፓርቲ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን በመተግበር የክልሉ ህዝብ በሰላም በልማትና በፖለቲካ ተሳትፎ ተጠቃሚ መሆን በመጀመሩ ሊደገፍ ይገባል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሰላሙን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል። የክልሉን ህዝብ ወክለው በፓርቲው አመራርነት ለሚሳተፉ አካላት ሀገራዊና ክልላዊ የአንድነት ምሶሶዎችን እንዲጠብቁም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የክልሉ ሴቶችን በመወከል ወይዘሮ ሂቡ አህመድ እንደተናገሩት፤ ሴቶች በፌዴራል ሥርዓቱ ያገኙትን መብት አጠናክሮ ለማስቀጠል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው። በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ ሴቶች ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን እየተካሔደ ያለውን የለውጥ ጉዞ ይደግፋሉ። በጅግጅጋ ከተማ እየተካሔደ ባለው በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በጅግጅጋ ከተማና አካባቢው የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። የብልፅግና ፓርቲን በመደገፍ በጅማ፣ በአዳማና፣ በቢሾፍቱ የድጋፍ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012