አቡዳቢ፡- “የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ላለፉት 25 ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ታስራ የቆየች ቤተክርስቲያንን አስፈትተዋል” ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ፣ ሊባኖስና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ዲሜጥሮስ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከዚህ በፊት ለስራ ከሚጓዙባቸው ሀገራት እስረኞችን በማስፈታት ወደ ሀገራቸው ይዘው እንደሚመለሱ ያስታወሱት አባ ዲሜጥሮስ፤ በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው ደግሞ ቤተክርስቲያንን ጭምር ማስፈታታቸውን ገልፀዋል።
ሊቀጳጳሱ በቦታው በርካታ ዓመታትን ማሳለፋቸውን ገልፀው፤ ባለባቸው የአምልኮ ቦታ እጦት ምክንያት እርሳቸውና ምዕመኑ በርካታ ችግሮችን ያሳለፉ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የቤተክርስትያን መስሪያ ቦታ በመፈቀዱ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ቤተክርስቲያኗ በኪራይ ቦታ ለሶስት ሰአታት ብቻ መንፈሳዊ አገልግሎትን ትሰጥ እንደነበር አስታውሰው፤ ታቦቱንም በመኖሪያ መንደሮች በማስቀመጥ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህ ሁኔታ ቤተክርስትያኗ በስደት ላሉ ምእመናን ላለፉት ዓመታት መንፈሳዊ አገልግሎት እንደሰጠች አመልክተዋል።
ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የፓትርያርክነት ዘመን አንስቶ እስከአሁን ድረስ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ጭምር ይህ የቦታ ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲቀርብ መቆየቱን የተናገሩት አባ ዲሜጥሮስ፤ ተቀባይነትን ሳያገኝ ከሁለት አስርት ዓመታትን በላይ ቆይቶ አሁን ፈቃድ መገኘቱ ለአካባቢው የእምነቱ ተከታዮች ትንሳኤ ነው ብለዋል።
ይህ የቤተክርስቲያን መስሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ትብብር ያደረጉ ሀገሮችንና ባለስልጣኖቻቸውን ያመሰገኑ ሲሆን፤ ለመላው የእምነቱ ተከታይ ምዕመናን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
ድልነሳ ምንውየለት