አዲስ አበባ፡- በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል አዳዲስ ማዋለጃ ክፍሎች ተዘጋጅተው አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም በውሃ እጥረት ምክንያት ወላዶች ታጥበው ለመውጣት መቸገራው ተገለጸ።
የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ታሪኩ ደሬሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በሆስፒታሉ በወር ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ እናቶች ይወልዳሉ። በሆስፒታሉ የውሃ አቅርቦቱ በጣም የተቆራረጠ ነው።
ለማዋለጃ ክፍሎች ተብሎ የተተከሉ የውሃ ማከማቻዎች ቢኖሩም በቀን አንድ ጊዜ ማታ የሚመጣው ውሃ ሊሞላቸው አልቻለም። በዚህም እናቶች ከወለዱ በኋላ ታጥበው ለመውጣት ተቸግረዋል።
እንደ ዶክተር ታሪኩ ገለፃ፤ ቀደም ብሎ እናቶች የሚወልዱበትን ስፍራ በመቀየር በአንድ ክፍል ውስጥ ሁሉንም ነገር እንዲጨርሱ የማድረግ አሰራር ተጀምሯል። ነገር ግን፤ በውሃ እጥረት ምክንያት ወላድ እናቶች ታጥበው መውጣት አልቻሉም። በተጨማሪም የማዋለጃ መሳሪያዎች በፍጥነት ስለማይታጠቡ አላስፈላጊ ጠረን የመፍጠር ሁኔታዎች አሉ።
በውሃ እጥረት ምክንያት የላቦራቶሪ አገልግሎት፣ የማዋለጃ ክፍል እቃዎች ቶሎ አለመዘጋጀት እና ለመሳሪያዎች እና ለቀዶ ህክምና የሚሆኑ ልብሶች የሚታጠብበት ላውንደሪ ስለማይሰሩና ዝግጁ ስለማይሆኑ ቀዶ ህክምናዎች እንደሚሰረዙና እንደሚራዘሙ ገልፀዋል። ሆስፒታሉ 120 ሺህ ሊትር ውሃ በቀን የሚስፈልገው ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የውሃ ችግሩን ለመፍታት ከ60 እስከ 70 ሺ ሊትር የሚይዙ ሮቶ ታንከሮች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
እንደ ዶክተር ታሪኩ አባባል፤ በከተማው በቂ የሆነ የውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ሆስፒታሎች የራሳቸውን የውሃ ጉድጓድ እንዲቆፈሩ መመሪያ ወርዷል። የአዲስ አበባ ጤና ቢሮም ሆስፒታሎች በጀት አስይዘው እንዲሰሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል። የጋንዲ ሆስፒታልም ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በዚህ ረገድ ቀድሞ የነበረውን የውሃ ጉድጓድ ጥገና ለማካሄድ የታሰበው በገንዘብ እጥረት ምክንያት አልተቻለም። በመሆኑም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ቆጣሪ ከማሳደግ ጀምሮ ውሃ ሲጠፋ በቦቴ እያመላለሰ ይገኛል።
በሆስፒታሉ የቧንቧ ጥገና ሰራተኛ አቶ ፈለቀ አበራ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በመስመር ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣው ውሃ በቂ አደለም። በዚህ ምክንያት ሆስፒታሉ ውሃ በሮቶ በማጠራቀም እየተጠቀመ ይገኛል። የተጠራቀመውም ውሃ በቁጠባ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የሚለቅቀው ውሃ ታንከሮችን ከመሙላት በዘለለ አገልግሎት መስጠት እንደማይችል ተናግሯረዋል። ውሃ የሚመጣውም ሌሊት ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት ስራ እስከመከልከል ደረጃ ይደርሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
መርድ ክፍሉ