በ15 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የወንድና የሴት ቦርሳዎችን በተለያዩ ዲዛይኖች አምርታ ለገበያ የምታቀርበው ጥሩወርቅ አሰፋ፤ የ“ጥሩ ዲዛይን” ባለቤት ናት። ጥሩወርቅ፤ በአሁኑ ወቅት የአምስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ባለቤት ሆናለች። በግሏ ወደ ስራው ስትገባ የዲዛይን ሙያ ስልጠና ወስዳ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በስሯ ስድስት ሰራተኞችን ቀጥራ በልደታ ክፍለ ከተማ በወረዳ አራት መንግስት በሰጣት ሼድ ውስጥ ስራዋን ትከውናለች።
ወረዳው የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገላት እንደሆነ የምትናገረው ጥሩወርቅ፤ጥሬ እቃ ማለትም የዚፕ፤ የቁልፍ እና በክል የሚባሉ የተለያዩ ምርቶች እጥረት እንዳጋጠማት ጠቅሳለች። ይህም በስራዋ ላይ ከፍተኛ የጥራት ችግር መፍጠሩን ተናግራለች። “ጥሬ እቃዎቹ የሚገቡት ከቻይና አገር በመሆኑ ከመርካቶ ነጋዴ ስንገዛው በጣም በውድ ዋጋ ነው። ከውድነቱም በላይ በምንፈልገው አይነትና መጠን አናገኝም” በማለት በምርቱ ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑንም ትገልፃለች።
ጥሬ እቃዎቹ ከውጭ የሚገቡት በኮንቲነር ደረጃ በስፋት በመሆኑ በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ በኮንቲነር ደረጃ የማስገባት አቅም የላቸውም። ስለዚህ መንግስት አራት አምስት ካምፓኒዎች በጋራ ሆነው ከውጭ የሚያስገቡበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ትናገራለች።
እንዲሁም መንግስት እራሱ ጥሬ እቃውን አስገብቶ ለኢንተርፕራይዞች የሚያከፋፍልበት መንገድ መኖር እንዳበትም ትጠቅሳለች። ይህም ችግሩን ከማቃለል ባለፈ ምርታማነትን በመጨመር በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና መጫወት ይቻላል በማለት ሀሳቧን ትቋጫለች።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን በየአመቱ በሚያዘጋጀው ኤግዚብሽን ላይ በተደጋጋሚ ተገኝተን ሽያጭ እንድናከናውን፤ እንዲሁም ከሸማቹ ህብረተሰብ ጋር እንድንተዋወቅ በማድረግ የገበያ ትስስር ፈጥሮልናል። የምትለው ሌላኛዋ የግል ኢንተርፕራይዝ የ“እቴነሽ እና እምወድሽ” የሳሙናና ዲተርጀንት ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ እቴነሽ ግርማ ናት። ማህበሩ እሷን ጨምሮ ሶስት ባለሙያዎች ይሳተፉበታል።
በቢሾፍቱ ከተማ በ2007 ዓ.ም ወደስራ ሲገቡ መነሻ ካፒታላቸው 15 ሺህ ብር ብቻ መሆኑን በመጥቀስ፤ ክልሉ የተለያዩ ድጋፎችን ያደረገላቸውና ከልማት ባንክ ጋርም እንዳስተሳሰራቸው፤ በአሁኑ ወቅትም ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ትናገራለች። ከዚህም በላይ ሳሙናውን የሚያመርቱበት ማሽን ከአራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል። ይህንንም መሳሪያ ልማት ባንክ በብድር ገዝቶ ያቀረበላቸው እንደሆነ ትናገራለች።
የሚያመርቱት ሳሙና ደረጃውን የጠበቀና እጅግ ጥራት ያለው መሆኑን የምትናገረው እቴነሽ፤ በቅድሚያ ምርት የጀመሩት በፈሳሽ ሳሙናዎች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ፈሳሽ ሳሙናን ጨምሮ የተለያዩ ደረቅ ሳሙናዎችን ማሽኑን በመጠቀም እያመረቱ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ታብራራለች።
ከሚያመርቱት ሳሙናዎች መካከልም የሬት ደረቅ ሳሙና ተጠቃሽ ነው። ‹‹እሬት አሁን አሁን ለበርካታ ችግሮች ማለትም ለጭርት፣ ፊት ላይ ለሚወጣ ሽፍታና ለሌሎችም ነገሮች ተፈላጊ በመሆኑ እያመረትን እንገኛለን በዚህም ብዙዎች ተጠቅመው ውጤታማ እንደሆኑ ግብረመልስ አግኝተናል›› ትላለች።
አንድ ከሬት የተዘጋጀ ደረቅ ሳሙና 25 ብር ሲሸጥ ሌሎች ሳሙናዎችን ደግሞ በፋብሪካ ዋጋ ስምንት ብር፤ አንድ ሊትር የልብስ ፈሳሽ ሳሙና 30 ብር፤ አንድ ሊትር ፈሳሽ የዕቃ ሳሙና 28 ብር እንዲሁም የእጅ ሳሙና አንድ ሊትር በ26 ብር ለነጋዴዎች እንደሚያስረክቡ ትጠቁማለች።
የገበያ ተደራሽነታቸውን በተመለከተ ምርቶቻቸውን በተለይም ደረቁን ሳሙና ለመርካቶ ገበያ እና ወደ ሀረር አካባቢም በስፋት እንደሚያቀርቡ ትናገራለች። “በተለይም እንዲህ አይነት ባዛር ላይ መሳተፋችን የበለጠ እንድንተዋወቅ የሚያደርግ በመሆኑ መልካም አጋጣሚ ነው” ትላለች።
ይሁንና ከዚህ በበለጠ ለመስራትና ውጤታማ ለመሆን ምርቶችን በስፋት ለማከፋፈል ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፤ እኛ ግን የገንዘብ እጥረት አለብን።” በማለት ወደፊት ብድር አግኝተው ምርቶቻቸውን በስፋትና በጥራት በማምረት ወደ ውጭ የመላክ ሰፊ ዕቅድ እንዳላቸው ትገልፃለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
ፍሬሕይወት አወቀ