አዲስ አበባ፡- በ2012 የመጀመሪያ ግማሽ በጀት ዓመት ወደውጭ ከተላከው ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 99 ነጥብ 86 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱ ተገለጸ።
በኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ባንቲሁን ገሰስ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2012 በጀት ዓመት በመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ከውጭ ንግድ ገቢ ለማግኘት 116 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ዕቅድ የተያዘ ሲሆን 99 ነጥብ 86 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ተችሏል።
ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር 30 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ ማሳየቱን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።
ለወጪ ንግዱ ገቢ መጨመር ምክንያት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል። በተጨማሪም በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተካሄደ መሆኑ፣ የኢንዱስትሪዎቹ የስራ ባህል እየዳበረ መምጣቱ እና ዘመናዊ አሰራርን መከተል፤ እንዲሁም የግብዓት አቅርቦቱ የተሻለ መሆኑ ውጤት እንዳስገኘ አመልክተዋል።
የኢንዱስትሪዎቹ የገበያ መዳረሻ ጀርመን፤ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ ቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች ክር፣ ጨርቅ ፤ ልብስና ባህላዊ አልባሳት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ባንቲሁን ማብራሪያ፤ አብዛኛውን የገበያ ድርሻ የያዙት የውጭ አገር ባለሀብቶች ሲሆኑ፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲፈጽሙ ከተያዘላቸው ስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እቅድ ውስጥ ስድስት ነጥብ 55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል።
ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ክፍት የሆኑ ፋብሪካዎች ቢኖሩም አቅማቸውን አሳድገው በጥራት፣ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት አመርቶ ለገበያ ከማቅረብ አኳያ ክፍተቶች መታየታቸውን ገልፀዋል። በአጠቃላይ፤ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩት ፋብሪካዎች ከ200 በላይ ሲሆኑ በፋብሪካዎቹ ከመቶ ሺህ በላይ የስራ እድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
ዳይሩክተሩ አክለውም፤ የፋብሪካ አመራር ባህሉ የሚጠበቀውን ያህል ያለመሆኑ፣ የሠራተኛ ፍልሰት፣ ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራራጥና አልፎ አልፎም ቢሆን የግብዓት አቅርቦት ማነስ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዘርፉ ቀደም ሲል ከነበረበት ጋር ሲነፃፀር አሁን ላይ የተሻለ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል ካለበት ችግር እንዲወጣ ሰፊ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
ወርቅነሽ ደምሰው