አዲስ አበባ ፡- የዳኞችን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፤ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ጉዳይ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በተያዘው እቅድ መሰረት 80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለዳኞች እንደሚተላልፍ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የዳኞችን ደመወዝ ጥቅማጥቅምና የመኖሪያ ቤቶች ጉዳይ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ይገኛል። ከዳኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ ግንባታው ከተጀመረ ብዙ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በውሉ መሠረት ለማከናወን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ፤ ለዳኞች እየተገነቡ ያሉት 278 ቤቶች ናቸው። በአሁኑ ወቅት 80 ቤቶች ማለትም 40 ባለሶስት መኝታና 40 ባለሁለት መኝታ ቤቶች ግንባታቸው የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የመብራትና የውሃ ጉዳይ በማጠናቀቅ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በቅርቡ ለዳኞች የሚተላለፍ ይሆናል። ሌሎች ቤቶች ግንባታቸው እንደተጠናቀቀ ይተላለፋሉ።
ዳኞች የዳኝነት ስራቸውን ለመስራት የሚያስችላቸውን ግብዓት ለማሟላት እንዲቻል የፍርድ ቤቱ አስተዳዳር፤ እንዲሁም የዳኞች ጉባኤ ከመቼው ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የዳኞች የመኖሪያ ቤትና ጥቅማ ጥቅም መከበር ዳኞቹ ጥራት ያለው ውሳኔ መስጠት እንደሚስችላቸው
በመጥቀስ፤ ተጠያቂነትም በዚያው አግባብ ተነጻጸሮ መምጣት ያለበት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። አያይዘውም ዳኞች ውሳኔ ሲወሰኑ የሥነ ሥርዓት ህጎችን በጣሰና አድሎን በሚያሳይ መልኩ ከሆነ በፍርድ ምርመራ ዳይሬክቶሬት እና በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ እየታየ ማስተካከያ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ፍርድ ቤቱ በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው ያለው” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ጠንካራ የሆነ የዳኝነት ተቋም ለመገንባት የምናደርገውን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ ከሌሎች አካላት በተለይ ጠበቆችና አቃቤ ህጎች የፍርድ ቤቱን የሪፎርም ስራ ተገንዝበው ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
ወርቅነሽ ደምሰው