አዲስ አበባ፡- የብሄራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት በወቅቱ ባለመሰብሰቡ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ከአንድ ሺህ 966 ደረጃዎች ውስጥ 98 ደረጃዎች ብቻ መፅደቃቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስማ ጅሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ አንድ ሺ 966 ደረጃዎች እንዲፀድቁ ለብሄራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት ቀርበዋል። ይሁን እንጂ፤ ምክር ቤቱ ወቅቱን ጠብቆ ባለመሰብሰቡ 98 ደረጃዎች ብቻ ፀድቀዋል።
በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ረቂቅ ደረጃዎች መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት አቶ ይስማ፤ በእርሻው ዘርፍ አዲስ 68 ደረጃዎች እና በማስቀጠል ደግሞ 182 ደረጃዎች መቅረባቸውን ገልፀዋል። በተጨማሪም በስድስት ወር ውስጥ በኮንስትራክሽን ዘርፍ 350 ደረጃዎች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ይስማ ገለፃ፤ በኬሚካል ዘርፍ በአዲስ 70 ደረጃዎችና በማስቀጠል ደግሞ 213 ደረጃዎች አጠቃላይ 283 ደረጃዎች ለምክር ቤቱ ቀርበዋል።
በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ ዘርፍ 18 አዲስ ደረጃ፣ የተከለሰ 21 ደረጃ፣ 129 ደረጃዎች ደግሞ እንዲቀጥሉ ቀርበዋል። በኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ 149 አዲስ ደረጃዎች፣ የተከለሱ 34 ደረጃዎች በአጠቃላይ 183 ደረጃዎች ቀርበዋል። በአካባቢ ደህንነትና ጤና ዘርፍ ደግሞ 60 አዳዲስ ደረጃዎች፣ የተከለሱ 29 ደረጃዎች፣ በማስቀጠል ደግሞ 24 ደረጃዎች አጠቃላይ 113 ደረጃዎች ቀርበዋል።
ደረጃ መሰረታዊ የሆነ ነገር በመሆኑ ኤጀንሲው አንድ ምርት ማሟላት የሚገባው መስፈርትና የህግ ማዕቀፍ እንደሚያወጣ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም፤ አምራች ድርጅቶች ደረጃ ጠብቀው እንዲያመርቱ ማሳሰቢያ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል። አምራቾች ደረጃውን የጠበቀ ምርት ሲያመርቱ ገበያ ውስጥ እንዲቆዩ ከማድረጉ ባለፈ ደንበኞችን ማስደሰት እንደሚችሉ አመልክተዋል።
ተቆጣጣሪ አካላት ደረጃዎች በአግባቡ ተግባር ላይ መዋላቸውን የማየት፤ የመቆጣጠርና የመከታተል ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ተጠቃሚውም ጥራት ያላቸውን ምርቶች ብቻ እንዲጠቀም፤ በተለይ መድሃኒትን የመሳሰሉ አስገዳጅ የደረጃ ምርቶችን ሲገዛ ምልክቶችን መመልከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012
መርድ ክፍሉ