አቡዳቢ፡- ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገራት ለመከበር አስቀድመው እርስ በእርሳቸው መከባበርን መለማመድ እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በልዩ ልዩ ምክንያት በችግር ውስጥ ከሚገኙ፣ ጥቃት ከደረሰባቸው እና በመጠለያ ውስጥ ከሚገኙ ሴት ኢትዮጵያውያን ጋር በችግሮቻቸው እና በመፍትሄዎች ዙሪያ ትናንት በአቡዳቢ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱም ኢትዮጵያውያኑ የደረሱባቸውን ችግሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ዜጎቹ በሚሰሩባቸው ሀገራት ተከብረው መኖር ይችሉ ዘንድ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ፣ ወደ አረብ ሀገራት የሚደረገው በደላሎች የሚፈፀም ሕገወጥ ጉዞ ሊቆም የሚችልበትን መንገድ መንግሥት እንዲያመቻች፣ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲዎች እውቅና እንዲኖራቸውና ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ፣ ቆንስላና ሚሲዮኖች ኮሙኒቲዎችን እንዲደግፉ፣ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ዜጎች በማህበራት
ተደራጅተው እንዲሰሩ፣ ያለጥፋታቸው በእስር ቤቶች ላሉ ዜጎች መፍትሄ እንዲፈለግና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በምላሻቸውም ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገራት ለመከበር አስቀድመው እርስ በእርሳቸው መከባበርን መለማመድ እና ከመጠላለፍ መውጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ጠቅመው ሀገራቸውን ለማሳደግ በሚኖሩባቸው ሀገራት የመደጋገፍና ጠበቃ መሆንን ሊያዳብሩ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
ሕገወጥ ደላሎች በሰዎች ዝውውር ላይ ብቻም ሳይሆን ሕገወጥ የጦር መሣሪያንም ወደ ኢትዮጵያ በማስገባትም ጭምር ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ ድርጊቱን ለመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ ነው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
እውቅና ያላገኙ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲዎች ከኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ጋር በመሆን መፍትሄ እንደሚፈለግላቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ የትምህርት ቤቶችን ግንባታና ሌሎችም የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ከመሪዎች ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ሀገራቸው መግባት የሚፈልጉ ዜጎች አብረዋቸው መሄድ እንደሚችሉ የገለፁ ሲሆን፤ በሀገራቱ ለመቆየት የሚፈልጉትን ደግሞ ጉዳያቸውን አስረድተው መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰሩ አረጋግጠውላቸዋል፡፡
በውይይቱ ከተገኙት ውስጥ 53 ያህሉ ሴቶች ከመጠለያ ወጥተው ችግራቸውን ለማስረዳት የተገኙ ሲሆን፤ መጠለያው በተለያየ መንገድ ችግር ደርሶባቸው የተገኙ ወገኖችን የሚያስተናግድ ነገር ግን እውቅና የሌለውና ካለው ሰፊ ችግር አንፃር ተጎጂዎችን ለማገዝ የተሰራ እንደሆነ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ተናግረዋል።
በውይይቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወደመካከለኛው ምሥራቅ የተጓዙ የልዑክ ቡድኖች፣ የኮሙዩኒቲ ተወካዮች እና በኢኮኖሚ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተገኙ ሲሆን ከተጎጂዎች ጋርም በጋራ ቁርስ በልተዋል፤ በችግሮቻቸው ዙሪያም ሃሳብ ተለዋውጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን ካቲት 8/2012
ድልነሳ ምንውየለት