አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ አዲስ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል አዳዲስ የክትባት ምርምሮችና ነባሮቹን ክትባቶች ለመጠቀም የተቋቋመውን ዓለም አቀፍ ጥምረት መቀላቀሏን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አዳዲስ በሽታዎችን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባት ምርምር ቅድመ ዝግጅት በሚያደርገውና የተገኙትን ክትባቶች በጋራ ለመጠቀም በሚሰራው ዓለም አቀፍ ጥምረት ውስጥ በሦስት ዓመት ሦስት መቶ ሺ ዶላር ለመክፈል በመስማማት ተቀላቅላለች።
ኢትዮጵያ ከሌሎቹ አገራት አንጻር በቀጣይ ሦስት ዓመታት ለማዋጣት የገባችው ቃል አነስተኛ ነው ያሉት ዶክተር ሊያ ጥምረቱ በቀጣይ ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ አዳዲስ ክትባቶችን ለማግኘት ምርምር የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ በምርምር የሚገኙትን ክትባቶች ለማምረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ኢትዮጵያ አዲስ ከሚገኘውም ክትባት በላይ በዓለም ላይ ቀደም ሲል የተሰሩ ክትባቶችን በጋራ ለመጠቀም ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት የጥምረቱ አባላት ተስምተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደምትሆን ገልጸው በአፍሪካ 98 በመቶ የሚሆነው ክትባት ከሌላ አህጉራት የሚመጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዳዲስ የወረርሽኝ በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት ሆነዋል ያሉት ዶክተር ሊያ እነዚህን በሽታዎች በጋራ ለመቋቋም የዓለም አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አዳዲስ ክትባቶችን ለማምረት ጥምረት ፈጥረዋል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት በጥምረቱ የገባች የመጀመሪያዋ አገር መሆኗን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
ጥምረቱ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በአጋር ድርጅቶችና አባል አገራት ገንዘብ መዋጮ ከሦስት ዓመታት በፊት በመቋቋም ለአዳዲስ በሽታዎች መከላከያ ጥናትና ምርምር እያደረገ ይገኛል። የድርጅቱ ትልቁ ግብም ለሚከሰቱ አዳዲስ በሽታዎች ክትባት መስራት ነው። ዓለም አቀፍ ጥምረቱ እንደኮሮና ቫይረስ ላሉ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በጋራ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግና በሚከሰቱበት ወቅት በአፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን ካቲት 8/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ