የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥትና ሕዝብ የሰጡትን ተልዕኮ፣ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ሁሉ በከፍተኛ ፅናትና ጀግንነት እንዲሁም በድል አድራጊነት ተወጥቷል። አሁንም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት እየተሰጡት ያሉትን ግዳጆች የሰላምና መረጋጋት ሥራዎችን በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እየተወጣ ነው።
አኩሪ የጀግንነትና የአሸናፊነት ባህል ያለው መከላከያ ሠራዊት ሀገርና ሕዝብ ክብርና ዕውቅና ይሰጡት ዘንድ ሠራዊቱም ለሕዝቡና ለሀገሩ ያለውን ታማኝነትና ፍቅር በመግለፅ ቃሉን እንዲያድስ በየዓመቱ ቀን ተቆርጦለታል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወሰነው መሠረትም የካቲት 7 ቀን የሠራዊት ቀን ተብሎ ይከበራል።
የሠራዊት ቀን በየዓመቱ መከበሩ ያለፈውን ጉዞ መለስ ብሎ ለማየት፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥና ወደፊት የሚሰጥን ተልዕኮ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ እሴቶቹን ተላብሶ በፅናት ለመወጣት እንደሚያግዘውም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አመልክቷል።
እንደ መግለጫው የዘንድሮ የሠራዊት ቀን በአንድ በኩል የዝግጁነት ደረጃውንና ዘመናዊነቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርበት፣ ቀጣይ ግዳጁንም በከፍተኛ ብቃት ለመፈፀም የሚያበቃውን ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ ማካሄዱን የሚያሳይበት ነው።
መከላከያ ሠራዊቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን ሰላም በፅናት እንደሚጠብቅ በዚህ አጋጣሚ እናረጋግጣለን ያለው መግለጫው ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎችና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራና ጠንክሮ በመስራት በታማኝነት፣ በሕዝባዊነትና በፍፁም ገለልተኝነት የሀገሪቱን ደህንነትና የሕዝቦቿን ሰላም ከማንኛውም ጥቃት እንደሚከላከልም አብራርቷል።
አምና ለ7ኛ ጊዜ የተከበረው የሠራዊት ቀን በዕዞችና ክፍሎች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ከቆየ በኋላ የማጠቃለያው በዓል በኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይልና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ወታደራዊ አዛዦችና አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት መካሄዱን ያስታወሰው መግለጫው በወቅቱም ከኅብረተሰቡ ጋር በነበረው የጋራ መድረክ ላይ ለግዳጅ አፈፃፀም የሚያግዙና ስንቅ የሚሆኑ በርካታ ጠቃሚ ሃሳቦች የተገኙበትን ሠራዊቱም የዝግጁነት ደረጃውንና የገነባውን አቅም ሕዝብ እንዲገነዘበው በማድረግ አስተማማኝ የሕዝብ ኃይል መሆኑን ያስመሰከረበት ነበር።
ዘንድሮም ለ8ኛ ጊዜ «የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም በፅናት እንጠብቃለን» በሚል መሪ ቃል ታስቦ የሚውለው በዓሉ በተቋሙ የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ተጠናክሮ በቀጠለበትና ውጤትም እየተመዘገበ ባለበት ወቅት ነው ተብሏል።
የሠራዊት ቀን በየዓመቱ በውይይት፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች የሠራዊቱን ዝግጁነት በሚያሳዩ ወታደራዊ ሰልፎችና ትርኢቶች ተከብሮ ይውላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
እፀገነት አክሊሉ