አዲስ አበባ፡- የመጀመሪያ ዙር ግንባታው የተጠናቀቀው የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ዛሬ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስ ጠት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስ ቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አሸብር ኖታ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ለኢትዮጵያ ስምንተኛው ደረቅ ወደብ ሆኖ ዛሬ ወደ ሥራ ይገባል። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ወረታ ከተማ የመጀመሪያ ዙር ግንባታው የተጠናቀቀው ደረቅ ወደብና ተርሚናል 100 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
እንደ አቶ አሸብር ገለጻ፤ የወደብና ተርሚናሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ለቀጣይ ግንባታዎች የሚሆን ቀሪ 17 ሄክታር መሬት ደግሞ ዝግጅት ተጠናቋል። ወደቡም በአሁኑ ወቅት ከ930 በላይ ዕቃ መጫኛ ኮንቴይነሮችን በአንድ ጊዜ የመያዝ አቅም አለው። ኮንቴነሮቹን በሁለትና በሦስት ረድፍ በመደራረብ መጠቀም ሲቻል ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ኮንቴይነሮችን ለማቆየት የሚያስችል አቅም እንዳለው ያሳያል።
አቶ አሸብር እንደተናገሩት፤ የወረታ ወደብና ተርሚናል በውስጡ ከኮንቴይነር ማስተናገጃ በተጨ ማሪ የተሽከርካሪ ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ ተከናውኖለታል። በተጨ ማሪም ሁለት ትላልቅ መጋዘኖች፣ የቢሮ አገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች፣ እና የባንክ አገልግሎት መስጫዎች እንዲሁም የሠራተኛ መዝናኛዎችን ይዟል። ከዚህ ባለፈ የራሱ የሆነ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድና የውሃ መስመር እንዲሁም መጠባበቂያ ጄነሬተርን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና ሌሎችም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታል።
ወደብና ተርሚናሉ ከባህር ዳር ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት እና ከጎንደር በ120 ኪሎ ሜትር ረቀት ላይ እንደሚገኝ የገለጹትን አቶ አሸብር፤ በሱዳን በኩል ላለው የወጪና ገቢ ንግድ መቀላጠፍ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል። ከሱዳን ጋር ያለውን የንግድ ትስስር ከማሳለጥም ባለፈ በንግድ መስመሩ የተቀላጠፈ የጉምሩክ አሠራርን በመዘርጋት ለአስመጪዎች እና ላኪዎችም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳ ገልጸዋል።
እንደ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መረጃ የወረታ ወደብና ተርሚናል ግንባታ ጥናት ከአስር ዓመታት በፊት ቢከናወንም በይፋ ሥራ የተጀመረው መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ላይ ነው። ከባህር ወለል በላይ በ1828 ሜትር ከፍታ ላይ በምትገኘው ወረታ ከተማ አቅራቢያ የተገነባው ደረቅ ወደብና ተርሚናሉ በተለይ በአካባቢው ለሚገኘው ከፍተኛ የሰሊጥ እና የሰብል ምርት የንግድ እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ታምኗል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
ጌትነት ተስፋማርያም