አዲስ አበባ፡- በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ እና በአሁኑ ወቅት የመጨረሻውን የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ የያዙ የኤር ባስ ኤ 350 አውሮፕላን ጥገናዎች ለማከናወን መመረጡን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ረታ መላኩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም የመጨረሻው ዘመናዊ አውሮፕላን ቴክኖሎጂ የያዘውን ኤርባስ ኤ 350 የተሰኘው አውሮፕላን ነው። የኤርባስ ኤ 350 አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ደግሞ በአፍሪካ የሚደረጉ የአውሮፕላኑን ጥገናዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲከናወኑ ፈቃደኝነታቸውን በማሳየታቸው አየር መንገዱ እንደ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
እንደ አቶ ረታ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሉት 14 ኤርባስ ኤ 350 አውሮፕላኖች ውስጥ አራቱ አውሮፕላኖች ከፍተኛ ጥገና በኢትዮጰያውያን ባለሙያዎች በሚገባ ማከናወን ተችሏል። በወቅቱ የኤርባስ ሰዎች በጥገናው መሳካት ላይ ስጋት የነበራቸው ቢሆንም ያለምንም ችግር ሥራው ተከናውኖ አውሮፕላኖቹ ለተጨማሪ አገልግሎት ውለዋል።
ይህንን የአየር መንገዱን ብቃት የተመለከቱ የኤርባስ ኩባንያ ሰዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥገና ብቃት ላይ ያላቸው መተማመን ጨምሯል። በዚህም ምክንያት አየር መንገዱን ለአፍሪካ የጥገና ማዕከል ሆኖ እንዲሠራ መርጠዋል። ይህም በቀጣይ ጊዜያት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ የገበያ አማራጭ የሚፈጥር ዕድል ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኦፕሬሽን መምሪያ ዋና ኃላፊ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ካሉት 14 ኤርባስ ኤ 350 አውሮፕላኖች በተጨማሪ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ አስር ኤርባስ አውሮፕላኖች እንዲሠሩለት ማዘዙን አስታውቀዋል።
በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ኤርባስ አውሮፕላኖች በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም በቀጣይ ጊዜያት ሊገዙ የሚችሉ አየር መንገዶች መኖራቸው ታሳቢ ሲደረግ ጥገናቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስር እንዲሆን መደረጉ ጥሩ የገበያ አማራጭ እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።
አፍሪካ ውስጥ የአውሮፕላኖች ጥገና ማዕከላት እጥረት መኖሩን የገለጹት አቶ መስፍን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በሰው ኃይል እና በመሳሪያ አቅም የተደራጀ በመሆኑ በአፍሪካ ከሚገኙ አየር መንገዶች በጥገና ብቃቱ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል። «ለራሳችን ብለን የምንገነባው አቅም ለአፍሪካውያን አየር መንገዶች ጭምር የሚተርፍ ጥቅም አለው» ብለዋል።
አየር መንገዱ በአነስተኛ ወጪ ብቃት ያለው አገልግሎት ለአፍሪካውያን መስጠት እንደሚችል እየተዋወቀ መምጣቱን ጠቅሰው፤በዚህ ረገድ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው እና በአየር መንገዶች የጥገና እና ስልጠና ጉዳዮች ላይ ባተኮረው የአፍሪካ አቪዬሽን ኮንፍራንስ ላይ ስለአየር መንገዱ የጥገና ብቃት እና አዋጭነት ለሌሎች አየር መንገድ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ገለጻ መደረጉን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡም በተካሄደው የአፍሪካ አቪዬሽን ኮንፈረንስ ወቅት ለ15 ዓመታት የሚቆይ የአውሮፕላን ቁሳቁስ ጥገናን በጋራ መሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከአቡዳቢው ኩባንያ ከሳናድ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ተፈራርሟል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
ጌትነት ተስፋማርያም