ወሊሶ፡- ከአዋሽ ወንዝ ሙላት ጋር በተያያዘ ክረምት በመጣ ቁጥር በጎርፍ ለሚጠቁት በኦሮሚያ ክላዊ መንግስት የኢሉና ዳዎ ወረዳዎች ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት አለመቻላቸው ተገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታየ ጉዲሳ ለበሪሳ ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ የአዋሽ ወንዝ በየዓመቱ በሚያስከትለው የጎርፍ መጥለቅለቅ ከቤት ንብረታቸውና ከመንደራቸው ከሚያፈናቅላቸው የዞኑ ወረዳዎች ውስጥ በዋናነት የኢሉና የዳዎ ወረዳዎች ተጠቃሽ ናቸው። በጎርፍ የሚፈናቀሉትን የወረዳዎቹን ነዋሪዎች
ለማቋቋም በየዓመቱ እርዳታ የሚደረግ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አላስቻለም፡፡
ችግሩ በየዓመቱ የሚከሰት የኢሉና ዳዎ ወረዳ ነዋሪዎች ችግር ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት እንደሚገባውም አቶ ታየ ተናግረዋል። በነዚህ ሁለት ወረዳዎች በየዓመቱ የሚከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ህብረተሰቡን ክፉኛ እያሳሳበ ያለ ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።
በአዋሽ ወንዝ አቅራቢያ ያለው የእርሻ መሬት ለምና ምርታማ ቢሆንም ተፈጥሯዊ አቀማመጡ ረባዳማ በመሆኑ በክረምት ወቅት በሚደርስበት የጎርፍ መጥለቅለቅ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን አስረድተዋል። በዚህ የተነሳም የአካባቢው እርሻ የሚስተጓጎል በመሆኑ አርሶ አደሮቹ ዕርዳታ ጠባቂ ለመሆን መገደዳቸውን ጠቅሰዋል።
በየዓመቱ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ህይወት እያመሰቃቀለና ቅሬታ እያስነሳ ያለውን ይህን ችግር ለመፍታትም የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን አቶ ታየ አስረድተዋል። በመሆኑም ጎርፉ ወደ እርሻ መሬቱ እንዳይገባ የመቀልበሻና የማስተንፈሻ ቦይ ቁፋሮ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፈው የአካባቢው ህብረተሰብ ከተረጂነት ወጥቶ እንዲያመርት ለማድረግና መሬቱም ጥቅም እንዲሰጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ አንዳንድ የልማት ስራዎች ለጊዜው ተጀምረው መቆማቸውን የተናገሩት አቶ ታየ ይህ ጅምር ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልተጠናቀቀ የከፋ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቅሰዋል። ጎርፉን የመከላከል ስራ ለኢሉና ዳዎ ወረዳዎች የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት ምክትል አስተዳዳሪው፤ ችግሩ በወቅቱ መፍትሄ ባለማግኘቱም እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ መቻሉን አስታውሰዋል።
«በየዓመቱ አርሶ አደሩ የሚያጣውና የሚደረግለት እርዳታ አይመጣጠንም» ያሉት አቶ ታየ፤ ቁርጠኛ የፖለቲካ አቋም ይዞ ለችግሩ እልባት መስጠት እንደሚያስፈልግ አስገንዝብዋል። እንደዚህ አይነቱ ማህበራዊ ቀውስ በወቅቱ መፍትሄ ካላገኘም ፖለቲካዊ መልክ ይዞ ሊመጣ ስለሚችል ከወዲሁ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በጎርፍ ለተጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎች በየጊዜው እርዳታ መስጠቱም ዜጎች በራሳቸው እንዳይተማመኑ፣ የጠባቂነት እና የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ የራሳቸውንም ሆነ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚጎዳ መሆኑን አቶ ታየ ጠቁመዋል።
ስለሆነም እንዲህ ዓነቱን እርዳታ ከማድረግ ይልቅ መሬታቸው አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያስችል ጉዳይ ላይ ትኩት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በመሆኑም የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው የአዋሽ ተፋሰስ በህብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን አደጋ ለማስወገድ መረባረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአዋሽ ወንዝ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በተለያየ ጊዜ የምግብና የዘር እህል እርዳታ ተሰጥቷል።
ይሁንና የአርሶ አደሮቹ መሬታቸው አገልግሎት እንዲሰጥ፣ እንዳይፈናቀሉ የሚያስችል ስራ ይሰራ በሚል የተነሳው ቅሬታ ተገቢነት አለው። የሚሰጣቸውም እርዳታ ዋስትና የሌለውና ዘላቂ መፍትሄ መሆን ስለማይችል ጎርፉን የመከላከል ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።
በዚሁ መሰረት ወንዙን ለማስተንፈስ በተደረገ ሙከራ አበረታች ለውጥ መታየቱን ገልጸው፤ በቀጣዩ ክረምት ችግሩ እንዳይባባስ ከወዲሁ ትኩረት በመስጠት ተፋሰሱን አቅጣጫ የማስያዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አዋሽ ተፋሰስ ከሚያስከትለው አደጋ ጋር በተያያዘ የሚነሳውን የህብረተሰብ ቅሬታም በአጭር ጊዜ ለመፍታት አስፈላጊው ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አቶ ዳባ አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
ዋሲሁን ተክሌ