«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ በግልፅ አሳይቶናል» -በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን
ዱባይ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው እድገት የራሳቸውን ጡብ በማስቀመጥ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ። በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ በግልፅ ያሳያቸው መሆኑን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተሰባሰቡና ከ15 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በዱባይ ሸባብ አልአህሊ ስታዲየም መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ «በህብር ወደ ብልፅግና» በሚል መርህ በተዘጋጀው ሥነሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና ተረጋግጦ ዜጎቿ በምቾትና ደስታ የሚኖሩበት ጊዜ ሩቅም ብርቅም አይደለም፤ ይልቁንስ ይህ ኑሮ የሰርክ ህይወት ይሆናል። በመሆኑም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው እድገት ያራሳቸውን ጡብ ሊያስቀምጡ ይገባል።
“በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ስትከበሩ ሀገራችሁ ትከበራለች፤ የእናንተ ስኬትም የወገናችሁ ስኬት ነውና ለሀገራችሁ የእድገት መሰረት የራሳችሁን ጡብ አስቀምጡ” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “ሲደመሩ አስፈሪ፤ በጋራ ሲቆሙ ደግሞ የሀገር ኩራት” ሲሉ ተናግረው፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የሀገር ለውጥ የሚረጋገጠው በተደመረ ክንድና ብልፅግና በመሆኑ በሚያልፍ እድሜ የማያልፍ ታሪክ እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
እንደ ዶክተር አብይ ገለፃ፤ በጥላቻ የበለጸገ፣ በፍቅርም የቆረቆዘ ህዝብ የለም፤ በመለያየት ያሸነፈ፣ በመተባበርም የከሸፈ ሀገር በታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም፤ በስንፍናና ሌብነት የከበረ፣ በትጋትና በደግነት የከሰረ ማህበረሰብም በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ቂምና ጥላቻ ተወግዶ በፍቅርና አንድነት መኖር ከተቻለ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ፈርጥ፣ የዓለም ኩራት ለማድረግ ጊዜው ሩቅ አይሆንም። ዜጎች መጪውን የብልፅግና ዘመን በማሰብ በጋራ ቢሰሩ፤ ባለስልጣናት ደግሞ ሳይሰርቁ ቢያገለግሉ፤ ሁሉም የሚያልማትን የሰለጠነች ኢትዮጵያ በጋራ እውን ማድረግ ይቻላል።
በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በህይወታቸው ተፅፎ ያልተነበበ ልምድና ትልቅ የህይወት ጉዞ እንዳላቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ልምድ በመጠቀም ጠንክረው እንዲሰሩና ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው የሀገራቸውን ብልፅግና እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል የራሳቸውንና የቤተሠቦቻቸውን ህይወት ለመለወጥ ብሎም የሀገራቸውን እድገት እውን ለማድረግ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ ክብራቸውና ጥቅማቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ለማድረግ መንግስት ከሀገራቱ ጋር በቅንጅት በመስራቱ ውጤት መገኘቱንና ቀጣይ ስራዎችም በትኩረት እንደሚከናወን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር ረጅም ዘመንን ያስቆጠረ መልካም ግንኙነት ያላት መሆኑን አስታውሰው፤ «በቋንቋ፣ በታሪክና በእምነትም መመሳሰላችን ግንኙነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እንዲሄድ አስችሏል፤ ይህንን መልካም አጋጣሚም ለሀገራችን ብልፅግና እና ለዜጎቻችን ክብር እንጠቀምበታለን» በማለት ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የቤተክርስቲያን መስሪያ ቦታ ስትጠይቅ ቆይታ አሁን ላይ መንግስት ባደረገው መልካም ግንኙነት ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች መንግስት መልካም ፈቃድ ተገኝቶ ጥያቄዋ መመለሱ መንግስት በዚህ አካባቢ ለሚኖሩት ዜጎቹ ያለውን ተቆርቋሪነትና ፍቅር ያሳየበት ስኬት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በዱባይ ከተማ ተገኝተው ያስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ በግልፅ እንዳሳያቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።
ከአቡዳቢ ከተማ የመጣችው ወጣት ረሂማ ሸረፋ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተገኙበት መድረክ አንድነት የታየበት እንደነበረና ንግግራቸውም ኢትዮጵያን ተለውጣ ለማየት ያላትን ጉጉት የጨመረባት መሆኑን ተናግራለች። ይህም በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ተስፋ የሚሠጥ በመሆኑ ሁሉም ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቃለች።
«ሰርተን ወደ ሀገራችን መመለስ የምንችለው ደህንነታችን ሲረጋገጥና ተከብረን መኖር ስንችል ነው» ያለችው ወጣት ረሂማ ፤ ይህንን እውን ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሄዱበት ያለው መንገድ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም አመልክታለች። በማሳያነትም ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተፈቀደው የአምልኮ ቦታ ለመከበራችን ትልቅ ምሳሌ ተደርጎ ሊታይ እንደሚችልም ገልፃለች።
ነዋሪነቷን በዱባይ ከተማ ያደረገችው ወጣት የትናየት በቀለም መድረኩ ኢትዮጵያዊነት የተቀነቀነበት እንደነበር ተናግራለች። በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ዜጎች ከዚህ በፊት ይስተዋል የነበረው በርካታ ችግራቸው ተፈቶና ጥቅማቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጻ፤ የነገዋን ኢትዮጵያ በጉጉት እየጠበቀች እርሷም የድርሻችን እንደምትወጣ ተናግራለች።
በተመሳሳይ ከዱባይ ከተማ የመጣው ወጣት ሙርሰላ ኪያር በበኩሉ፤ በስታዲየሙ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው በማየቱ ደስታ እንደተሰማው ገልፆ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ለመለወጥና ወደ ብልፅግና ለማሻገር እየሰሩት ያለውን ስራ አድንቋል። በዱባይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግርም በሀገር ግንባታው የድርሻውን እዲያበረክትና ይበልጥ እንዳነሳሳው ተናግሯል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይ እውን ሆኖ የምንመኛት ኢትዮጵያን ለማየት ፍቅርን ማስቀደምና ቂምን በይቅርታ መሻገር እንደሚገባ ተናግረው ለሀገር ሰላም መረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
ድልነሳ ምንውየለት