– የፓርቲዎች የሴቶች ተሳትፎ 10 በመቶ ብቻ ነው
አዲስ አበባ ፡- ቀድሞ በተደረጉ ምርጫዎች የተሳተፉ የምርጫ አስፈፃሚዎች በነሐሴ ወር በሚደረገው በስድተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደማይሳተፉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። እስካሁን የፓርቲዎች የሴቶች ተሳትፎ 10 በመቶ ብቻ መሆኑን አመለከተ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት እንደተገለጸው፤ ከዚህ በፊት አስፈፃሚ የነበሩ ሰዎች ላይ አመኔታ ስለሌለ በምርጫ 2012 እንዳይሳተፉ ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ከዚህ በፊት አስፈፃሚ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ጥፋተኛ ናቸው ማለት አይደለም፤ እንዳይሳተፉ የተደረገው ግን ጥርጣሬን ለማስወገድ ነው። ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲነሱ የቆዩ ቅሬታዎች የሚያሳዩት ከዚህ በፊት የነበሩ አስፈፃሚዎች ካሉበት ገለልተኛ አይሆንም የሚል ነው።
የምርጫ አስፈፃሚዎችን ምልመላ በተመለከተም በመራጩ ማህበረሰብ ውስጥ አስተማሪ የነበሩና በገለልተኝነታው የሚታወቁ ሰዎች የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደሚሆኑ ሰብሳቢዋ ገልፀዋል። ለህዝብና ቤት ቆጠራ ሥልጠና ወስደው የነበሩም በተመሳሳይ ለአስፈፃሚነት እንደሚመለመሉ ተናግረዋል። በአገሪቱ ውስጥ ገለልተኝነትን የሚያረጋግጥ ዘመናዊ አሰራር ያለው ተቋም ስለሌለ ያለው አማራጭ ገለልተኝነታቸው የሚጣራው በማህበረሰቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ ያለው ፓርቲ ተጨባጭ መረጃ ካለው ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል የገለጹት ወይዘሪት ብርቱካን፤ ፓርቲዎች እስከ ወረዳ ድረስ ወርደው ከህብረተሰቡ ጋር መገናኘትና መረጃ መሰብሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ‹‹የትኛው የምርጫ አስፈፃሚ ችግር እንዳለበትና የትኛው እንደሌለበት ወርደው ማጣራት አለባቸው። የምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኛ ካልሆኑ የሚደረገው ምርጫ ከንቱ ይሆናል›› ብለዋል።
በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የስነ ምግባር አዋጁን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት የሴቶች ተሳትፎ 10 በመቶ ብቻ መሆኑን ቦርዱ በሪፖርቱ አመልክቷል።
ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመጡት ወይዘሮ ህሊና አሥራት ሪፖርቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፤ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት በነበሩት ውይይቶች ለሴቶች ልዩ ድጋፍ መደረግ እንዳለበት ተገልጾ ነበር፤ ይሁንና አሁንም ገና 10 በመቶ ብቻ መሆኑ የውድደሩን ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል።
ችግሩ ከፓርቲዎች ይሁን ከምርጫ ቦርድ ተለይቶ መቀረፍ እንዳለበት ያሳሰቡት ወይዘሮ ህሊና፤ 50 በመቶው የህብረተሰቡ ክፍል ሴቶች በሆኑበት ሴት ተመራጭ አለመኖር ማግለል እንደሆነ ገልፀዋል። አሁንም በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮችና በመገናኛ ብዙኃን የሚታዩት ወንዶች መሆናቸው ሲታይ ልዩ ድጋፍ የተባለው ተቀባይነት እንዳላገኘ አመልካች መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባል ዶክተር ጌታሁን ካሳ እንደገለጹት፤ የሴቶችን ተሳትፎ አሃዝ መግለጽ ያስፈለገው ዝቅተኛነቱን ለማሳወቅና ቦርዱን እንዳሳሰበው ለመግለጽ ነው። በህጉ ውስጥም ይህን ያህል አምጡ ብለው በቁጥር ከማስቀመጥ ይልቅ አበረታች መንገዶችን ለመጠቀም ታስቦ ነበር። አመራር ሴቶችን ለሚያቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት ብዛት መሰረት በሚሰጥ የገንዘብ ድጎማ ድጋፍ የማድረግ አሰራር አለ፡ ነገር ግን አሁንም በቂ የፆታ ተዋፅኦ አለመኖሩ በቀጣይ ሊሰራበት ሚገባ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ መረጃ የሚያሰባስብ 2 ሺ 391 የሰው ሃይል አሰማርቷል። በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍም ለምርጫ የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ተዘጋጅተዋል። በክረምት ወቅት መካሄዱ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅእኖ በተመለከተም ከብሄራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር እየተሰራ መሆኑን ሰብዋቢዋ ተናግረዋል።
ትናንት በተደረው ውይይት፤ የ2012 አገር አቀፍ ምርጫ ተከልሶ በቀረበው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የድምፅ መስጫ ቀን ነሐሴ 23 ቀን ሆኗል። በሌላ በኩልም ቦርዱ አርማውን መቀየሩን ይፋ አድርጓል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
ዋለልኝ አየለ