- ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ብሄራዊ ጥቅሟን እንደማታስነካ
- – በቻይና ለሚገኙ ከ300 በላይ ተማሪዎች መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ
- – 128 ኢትዮጵያውያን እስረኞች ከታንዛኒያ ወደ አገራቸው መግባታቸውን አስታወቀ
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በሚመለከት ከግብፅና ከሱዳን ጋር እያደረገች ባለችው ድርድር እስከመጨረሻው ድረስ ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቃ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኮረና ቫይረስ መነሻ በሆነችው በቻይናዋ ውሃን ግዛት ለሚገኙ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝና በታንዛኒያ ዳሬሰላም በሦስት እስር ቤቶች የነበሩ 128 ኢትዮጵያውያንን ከእስር በማስፈታት ትናንት ወደ አገራቸው መግባታቸውን ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ እንዳስታወቁት፤ እስከአሁን ድረስ በሦስቱ አገራት ሲደረግ በነበረው ድርድር ይሄነው የሚባል ውጤት ላይ አልተደረሰም። ኢትዮጵያ ወደፊትም በምንም መልኩ ብሄራዊ ጥቅሟን ሳታስነካ የምትቀጥል ይሆናል።
የህዳሴ ግድቡን በሚመለከት ሦስቱ አገራት ባሉበት በዋሽንግተን በሚካሄድ ድርድር ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ህጋዊ ሰነድ በመዘጋጀት ላይ እንደነበርና ዝርዝር የሆኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በህጋዊ ሰነዱ ላይ ለማካተት ጥረት እየተደረገ እንደነበር አቶ ነብያት አስታውሰዋል።
የህግ ሰነዱ እስከትላንት ድረስ ለፊርማ በሚበቃ ደረጃ ዝግጁ እንዳልነበርና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ ነጥቦች ባልተዘጋጁበት ሁኔታ በምንም መልኩ ስምምነቱን እንደማትፈርም ማስታወቋን አስረድተዋል።
አቶ ነብያት በአደራዳሪዋ አሜሪካና በተደራዳሪዎቹ አገራት ኢትዮጵያ ተፅእኖ እየደረሰባት ስለመሆኑ በጋዜጠኞች ተጠይቀው ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ ቢመጣም አስቀድማ በያዘችው አቋም እንደምትጸና፣ ድርድሩ መርህን መሰረት ያደረገ እንደሚሆንና ስምምነቱ የሚፈፀመውም የአገሪቱን ጥቅም ማስጠበቁ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ ከኮረና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በቻይና ያሉ ኢትዮጵውያንን በሚመለከት መንግሥት ቫይረሱ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ግብረኃይል አቋቁሞ ዜጎቹ ከበሽታው እንዲጠበቁና ህይወታቸውን ለመታደግ ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ የቫይረሱ መነሻ በሆነችው በቻይና ሁቤ ክፍለ ሀገር ውሃን ከተማ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ጋር በተያየዘ ምንም ዓይነት ችግር እንዳያጋጥማቸው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል የቻይና መንግሥት ከውሃን ከተማ መውጣትም ሆነ መግባት የከለከለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥያቄ ያቀረቡ ዜጎቹን በአፋጣኝ ማውጣት አለመቻሉን የጠቆሙት አቶ ነብያት፤ ተማሪዎቹ ባሉበት ዩኒቨርሲቲ የምግብም ሆነ የሌሎች ግብዓቶች እጥረት እንዳያጋጥማቸው ከቻይና መንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን፣ በቅርቡም መንግሥት ለተማሪዎቹ የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቤጂንግ ከሚገኘው ከኢትዮጵያ ኤምባሲና ከተማሪዎች ማህበር ጋር በአፈፃፀሙ ላይ በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
አቶ ነብያት በመግለጫቸው እንደተናገሩት በትናንትናው ዕለት በታንዛኒያ ዳሬሰላም ኡኮንጋ፣ ካጋሬና ሙሶማ እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ 128 ኢትዮጵያውያን በተደረገው ድርድር ከእስር በማስፈታት ወደአገራቸው እንዲገቡ ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአቡዳቢና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዜጎችን ጉዳይ በሚመለከትም ከአገራቱ መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፓምፒዮ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
ማህሌት አብዱል