አዲስ አበባ፡- ከኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አጋሮች መካከል ህንድ ሁለተኛ ትልቁን ድርሻ መያዟን እና በኢትዮጵያ ያለው በህንዳውያን የሚመራው ኢንቨስትመንት አራት ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት እና በህንዱ «አይቲ ሚ አፍሪካ» ተቋም አማካኝነት የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ኤግዚቢሽን ትናንትና በይፋ ተከፍቷል። በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ እንደገለጹት፤ ህንዳውያን በተለያዩ የጨርቃጨርቅ፣ ግብርና፣ በጤና ዘርፍ እና በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው በመስራታቸው ህንድ ሁለተኛ ትልቋ የኢንቨስትመንት አጋር ሆናለች።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በህንድና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እ.አ.አ በ2017 እስከ 18 ባለው ጊዜ ውስጥ 1 ነጥብ 27 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ከሆነም ኢትዮጵያ በብዛት ከውጭ ምርቶችን ከምታስገባባቸው ሀገራት መካከል ህንድ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ከኢትዮጵያ ገቢ ንግድ 10 ከመቶ በላይ ድርሻ አላት። በቀጣይም በጨርቃጨርቅ ዘርፎች ህንዳውያን ባለሀብቶች ቢሰማሩ ከግብዓት አቅርቦት እና ከታክስ ድጋፍ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ምቹ ሁኔታ አለ። ይህም የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር የበለጠ ለማሳደግ ይረዳል።
በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ሁለት ሺ ዓመታት በላይ የዘለቀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫ ናቸው። በጥንት ዘመን የተጀመረው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ እያደገ ቢሆንም ሁለቱንም ሀገራት የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት አማራጭ እና የተፈጥሮ ሀብት በርካታ መሆኑን በመጥቀስ ህንዳውያን በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ፋብሪካዎችን እንዲገነቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የህንዳውያን ባለሀብቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል። አሁንም የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በንግድ ሽርክና ከህንዳውያን በጋራ ሊሰሩ የሚችሉበትን እድል የሚፈጥር ነው።
በተለይም በጨርቃጨርቅ ዘርፍ በርካታ ባለሀብቶች በአዲስ አበባ በመገኘታቸው በቀጣይ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ ሊያጠናክሩ የሚችሉ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ያለውን የጨርቃጨርቅ ምርት የጥራት፣ የባለሙያ እና የቴክኖሎጂ ችግርን ለመቅረፍ እንዲረዳ ከህንዳውያኑ ጋር በጋራ መስራት አዋጭ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል።
ትናንትና የተከፈተው የጨርቃጨርቅ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ኤግዚቢሽን እስከዛሬ ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፤ ከ15 ሀገራት የመጡ 175 ኩባንያዎች እየተሳተፉበት ይገኛል። ከተሳታፊ ኩባንያዎቹ መካከል ደግሞ ግማሽ የሚጠጉት ከህንድ የመጡ ናቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012
ጌትነት ተስፋማርያም