አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ የሚገኙ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች በአግባቡ ካለመያዛቸው የተነሳ አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ባህል፣ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ስዩም ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፤ በከተማዋ የሚገኙ ጥንታዊ ቤቶች በቅርስነት ይለዩ እንጂ አስፈላጊው ጥበቃ፣ እድሳትና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ አደጋ ላይ ናቸው።
በመልሶ ማልማት፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች አብዛኞቹ ቅርሶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዱ ነው ያሉት አቶ ደረጀ ለግለሰቦች፣ ኃላፊዎችና ሌሎች በመኖሪያ ቤትነት የተሰጡ፣ ለማሰልጠኛነትና ሌሎች አገልግሎቶች እየዋሉ ያሉ ቅርሶች በወቅቱ ዕድሳት የማይደረግላቸው በመሆኑ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በቅርስነት በተለዩት ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩት ሰዎች ሌላ ቤት ተፈልጎ እንዲሰጣቸውና በመመሪያው መሠረት በቢሮው አስተዳደር ስር ሆነው አስፈላጊው ሁሉ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ለሚመለከተው ብናመለክትም እስካሁን ያገኘነው ምላሽ የለም ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በከተማዋ ንብረትነታቸው የግለሰብ የሆኑ ነገር ግን በቅርስነት የተመዘገቡ በርካታ ቤቶች አሉ። ይሁን እንጂ በግለሰቦቹ አቅም ማነስ ምክንያት ሊያሳድሷቸውና ወደ ቱሪስት መስህብነት ሊቀይሯቸው አልቻሉም። እንዲያሳድሱ ሲነገራቸውም በቂ ገንዘብ የለንም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡት።
እስከዛሬ ድረስም ካሉት የቤት ቅርሶች አስሩ ከነጭራሹ ታድሰው አያውቁም። በመሆኑም በከተማዋ ያሉ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችን በአግባቡ ለቱሪስት መዳረሻነት ተጠቅመንባቸዋል ማለት አይቻልም።
በቤቶች ኮርፖሬሽን ስር ብቻ 54 በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ «ወይ መልሱልንና እኛ እንጠብቅና እንንከባከባቸው፤ ወይም እናንተ ጠብቋቸው እያልን በየጊዜው ብንጻጻፍም አመርቂ ምልሽ ሊገኝ አልቻለም» ብለዋል፡፡
አቶ ደረጀ እንደገለጹት፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች የሁሉም አካል ቅርሶች ናቸው። በመሆኑም ሁሉም አካል ሊንከባከባቸው፣ ሊጠብቃቸውና ለቱሪስት መስህብነት ሊያውላቸው ይገባል።
እድሳት ሲደረግ ቅርሶቹ ላይ ጉዳት አይደርስም ወይ? የሚል ጥያቄ ለአቶ ደረጀ አቀረብንላቸው አንድ ቅርስ ከመጠገኑ በፊት ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል።
በተጠናው መሰረት ለዕድሳቱ ጨረታ ይወጣል። ተወዳድሮ ያሸነፈ በሚመለከተው አካል ከፍተኛ ክትትል ስር ሆኖ እድሳቱን በጥናቱ መሰረት ያካሂዳል። ጨረታው የሚወጣውም ሆነ የሚወዳደሩት በዘርፉ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ያላቸው ተቋራጮች ብቻ ናቸው። በመሆኑም በእድሳት በኩል ያጋጠመ ችግር የለም፤ ሁሉም እስካሁን የታደሱት የነበራቸውን ይዘት እንደጠበቁ ነው የታደሱት በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ደረጀ እንዳሉት፤ቀደም ሲል በመንግሥት ተቋማት ሁሉ ሳይቀር ታሪካዊና ቅርስ የሚሆኑ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ይህ ክስተት ዳግም እንዳይፈጠርም ለሁሉም አካላት በከተማዋ ያሉ ቅርሶችን፣ መገናኛ ቦታቸውንና ሌሎች መረጃዎችን ሁሉ በጽሑፍ አሳውቀናል። ይደገማል ብለን አናስብም። አሁን ሌላ ሦስተኛ ወገንም በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤው እንዲሳተፍ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ ከ440 በላይ ታሪካዊ ቅርሶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ350 በላይ የሆኑት ቤቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥም ከ200 በላይ የሚሆኑት በአራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ግርማ መንግሥቴ