– መቆጠብን ባህል ማድረግ ችለዋል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ሥራን ከማማረጥ የአስተሳሰብ ችግር በመላቀቅ ማንኛውንም ሥራ ሳይንቁ መስራት ከመቻላቸውም በላይ መቆጠብን የዕለት ከዕለት ተግባራቸው ያህል ባህል ማድረጋቸውን ገለጹ።
ከፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር ተጠቃሚዎች መካከል በሞዴልነት የሚጠቀሱት ወይዘሮ አስቴር አበራ፣ ወይዘሮ መሰረት ጌታቸው፣ ወይዘሮ ትዕግስት ገብረመድሕን፣ አቶ ታደሰ ደገፋ እና አቶ ሱራፌል ነዋይ እያንዳንዳቸው ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ዕድሜ ልክ አብሮ የኖረውና ሥር የሰደደው ሥራን የመናቅና የማማረጥ ችግር እንዲሁም ይሉኝታ በርካታውን ነዋሪ የሚላስ የሚቀመስ አሳጥቶታል። እነሱም ከዚህ አስተሳሰብ ችግር መላቀቃቸውን ገልጸዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ጥቂት ሳንቲም ምናልባትም አስር ብር የማይደርስ ብር በየጊዜው እየሄዱ ባንክ ቤት ማስቀመጥና መቆጠብ የሚያሳፍር ተደርጎ ከመቆጠሩም በላይ ለድሃ ያልተፈቀደና ትርፍ ገንዘብ ላላቸው የተዘጋጀ አድርጎ የማሰብ ችግሮች በሰፊው መኖራቸውን ገልጸዋል። እነዚህን የአስተሳሰብ ችግሮች መሻገር አለመቻል ለድህነትና ለሥራ አጥነት ኅብረተሰቡን እየዳረገ ነውም ይላሉ።
ወይዘሮ አስቴር አበራ እንደተናገሩት፤ ምንም ዓይነት ገቢም ሆነ ረዳት እንደሌላቸው በማህበረሰቡ ተለይተው በልማታዊ የሴፍትኔት ፕሮግራም ተካተው ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም በአካባቢ ልማት በመሳተፍ በየወሩ ከሚያገኙት 900 ብር ክፍያ ከ30 በመቶ በላይ በየወሩ ሳያሰልሱ እንደሚቆጥቡ ገልጸዋል። ነገር ግን ክፍያው ከቀረፈላቸው የዕለት ችግር በላይ ማንኛውንም ሥራ ያለአንዳች መሸማቀቅ፣ ሀፍረትና ይሉኝታ መስራት የሚያስችል አስተሳሰብና በራስ መተማመን እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።
‹‹ትንሽ ገንዘብ ይዞ ባንክ ቤት መሄድና ትንሽ ገቢ በሚያስገኙ በሚባሉ ሥራዎች ላይ መሰማራት እስከአሁን ድረስ እንደ ነውርና እንደመዋረድ ይታያል›› የሚሉት ወይዘሮ መሰረት ጌታቸው፤ ይሄ ወገኖቻችንን ሰርተው እንዳይበሉ ያደረገና ሀገርንም ማደግ እንዳትችል ሰቅዞ የያዘ ኋላቀር አስተሳሰብ እንደሆነ ተናግረዋል። አሁን ይሄ ፕሮግራም በመምጣቱ በተለይም ለሴቶች ከእንዲህ ዓይነት የአስተሳሰብ ችግር መላቀቅ እንዲችሉ አድርጓቸዋል፤ ሥርዓት ባለውና በዘመናዊ መንገድ መቆጠብንም እንደተማሩበት አስረድተዋል።
አቶ ታደሰ ደገፋ በበኩለካቸው፤ ለድህነት የዳረገን የአስተሳሰባችን ችግር እንጂ የሥራ እጦት እንዳልሆነ ተናግረዋል። አሁን ከእነዚህ ችግሮች ፈልፍለው መውጣትና ዓይናቸውን መግለጥ እንደጀመሩ የሚናገሩት አቶ ታደሰ፤ በሴፍትኔት ፕሮግራሙ ባገኟቸው አጫጭር ሥልጠናዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር መቻላቸውን ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ እንደሚለወጡ ጭምር ተናግረዋል። ከፕሮግራሙ ያተረፉት የሥነልቦና ድፍረትና ማንኛውንም ሥራ ሳይንቁ ሰርቶ ገቢ የማግኘት ብቃት እንደሆነም ተናግረዋል።
ሥራን ከማማረጥና ከመናቅ በሽታ መላቀቅና ከሚገኘው ሳንቲም ለሆዴ አልበቃኝም ከሚል አስተሳሰብ ወጥቶ መቆጠብ ግድ እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ ታደሰ፤ የማህበረሰቡ በተለይ ደግሞ የወጣቱ ዋና ችግር ይሄ እንደሆነ አስገንዝበዋል። ፈሳሽ ሳሙና (ላርጎ) አምርተው ለገበያ በማቅረብ ከገቢያቸው እስከ አስተሳሰባቸው ድረስ ማደጉንም አክለው ገልጸዋል። በመሆኑም በዚህ ዓመት ከፕሮግራሙ በመመረቅ ለሌሎች ምንም ዓይነት ገቢ ለሌላቸው ሰዎች እንደሚለቁ ጠቁመዋል።
«የሴፍትኔት ፕሮግራም ከሚያስገኝልኝ የዕለት ጉርስ በላይ ማንኛውንም ሥራ ሳልንቅ አክብሬ በመስራት ገንዘብ ማግኘት እንደምችል ያረጋገጥኩበት እና ሌሎች አይሰራም የሚሉኝን ሰዎችም ማሳመን (ማስተማር) የቻልኩበት ነው» የሚሉት አቶ ሱራፌል ነዋይ፤ ማህበረሰቡ ሥራን የሚመርጥበት ሚዛን ከገቢ አንጻር ሊሆን ይገባል፤ መቆጠብ ከትርፍ እንዳልሆነም ማወቅ አለበት። በይሉኝታ የታጠረውን አስተሳሰቡን ቀርፎ ገቢውን ማሳደግ እንጂ ሌላ የድሕነት መፍትሄ አለመኖሩን አስረድቷል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ሙሐመድ ሁሴን