አዲስ አበባ:- በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) የተመዘገቡና በዓለም ቅርስነት እውቅናን ያገኙ የማይዳሰሱ ቅርሶች በአግባቡና በጥንቃቄ የማይያዙ ከሆነ እውቅናው ሊሰረዝ እንደሚችል ተነገረ።
ምንም እንኳን በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች መመዝገባቸው አስደሳች ቢሆንም ቅርሶቹ እስከ ዛሬ የነበሩበትን ይዘትና ማህበራዊ ፋይዳ ይዘው የማይቀጥሉ ከሆነ ሊሰረዝ፤ እውቅናውም ሊነጠቅ እንደሚችል ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
በባለሥልጣኑ የባህል አንትሮፖሎጂስት የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ግርማ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረትና ልፋትን የጠየቀ ሲሆን ይህንን ምዝገባና እውቅና አስጠብቆ ለማቆየትም የሁሉንም የጋራ ጥረት ይጠይቃል።
አንድ በዩኔስኮ የተመዘገበና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ቅርስ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን የማይጥስና በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት ግጭቶችን የማያስከትል፣ የመዘገበውን አካል ደንብና መመሪያ የሚያከብር፣ ፍፁም ሰላማዊ፣ ባህላዊም ሆነ መንፈሳዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ እንዲቀጥል፣ በየትውልዱ እየዳበረ በመሄድ (Recreation) ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ፣ የሕዝቦችን አብሮነት የማይነካ፣ ሰላማዊ፣ ልማትን የማያደናቅፍ ወዘተ ሆኖ ሊቀጥል ይገባል የሚሉት አንትሮፖሎጂስት ገዛኸኝ ይህ እንዲሆን የሁሉም ኅብረተሰብና ተቋማት የጋራ ጥረት እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህ ካልተደረገ አንዳንድ አገራት የደረሳቸው ዕጣ ፈንታ ሊገጥመን እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ገዛኸኝ ቤልጂየም የዚህ ዓይነቱ የመሰረዝ ክፉ ዕድል የደረሰባት አገር መሆኗን በምሳሌነት ይገልፃሉ።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የአደባባይ በዓላት ከአውዳቸው ውጪ ወደ ገበያነትና ሌሎች ከአላማው ላፈነገጡ ጉዳዮች ከዋለ፤ ሲመዘገብ የነበረውን ገፅታ ከቀየረ፣ ቱሪስቶችን ከማስተናገድ አኳያ ያለው ሁኔታ ከተበላሸ ወዘተ ምዝገባው እንዲሰረዝ የማድረግ ዕድልን ስለሚያመጣ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ያሉት አቶ ገዛኸኝ ለዚህም እከሌ ከእከሌ ሳይባል ከእያንዳንዱ ሰው፣ ተቋማት፤ በተለይም ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ኪዮስኮችን የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፤ የበዓሉ ታዳሚዎች፣ ሚዲያው ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉና በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀሱ ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ።
የቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገብ የሚያስገኘው ጥቅም አለ ወይ? ለተባሉትም በርካታ ጥቅሞች ያሉት መሆኑን የተናገሩት አንትሮፖሎጂስቱ ለምሳሌ የጥምቀት በዓል ገና ከመመዝገቡ በቱሪስት ቁጥር መጨመር፣ በገፅታ ግንባታ፣ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሽፋን በማግኘት፣ በዓሉ ከድሮው በበለጠ በደመቀ ሁኔታ መከበሩ ወዘተ ያስገኛቸው ጥቅሞች መሆናቸውን የተናገሩት አንትሮፖሎጂስቱ በአግባቡ ከያዝነው ገና ከዚህ የበለጠ ጥቅም እንደሚያስገኝልንም ተናግረዋል።
በቅርቡ በተካሄደው 14ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጉባኤን ላይ አንዱ ውሳኔ የጥምቀት በዓል ዓለምአቀፍ ቅርስ መሆኑን ተከትሎ ድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ መገለፁ ነውና ድጋፉ ምን ምን እንደሆነ እንዲገልፁልን ጠይቀናቸውም «በመሰረቱ ለማይዳሰሱ ቅርሶች የገንዘብ ድጋፍ አይደረግም።
የሚደረገው ድጋፍ ሥልጠና የመስጠት፣ ማማከር፣ በአባል አገራት መካከል መልካም ግንኙነትን በመፍጠር መረዳዳትና ልምድ መለዋወጥ እንዲኖር ማድረግ፣ በጉባኤዎች ላይ እንድንገኝ ማድረግና የመሳሰሉት ሲሆኑ እኔም በዘንድሮው ጉባኤ ላይ ልሳተፍ የቻልኩት በዚሁ አግባብ ነው።» ሲሉ መልሰዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ግርማ መንግሥቴ