አዲስ አበባ:- በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የባህል ማዕከላት የጋራ እሴት ላይ አተኩረው በመስራት የጋራ መግባባት መፍጠርና ሰላምን ማጠናከር ላይ መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ።
ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ከተገኘው መረጃ ለመገንዘብ እንደተቻለው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የባህል ማዕከላት እንዲቋቋሙ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት የተቋሙ ማህበረሰብ፤ በተለይም ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን፣ የየራሳቸውንና የሌላውን ማንነትና ባህሉን ወዘተ እንዲያውቁና የጋራ ማንነታቸውን በውል በመገንዘብ ተግባብተው፣ ተቻችለውና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ታስቦ ነው።
በዩኒቨርሲቲው የባህል ማዕከል ዳይሬክቶሬት የአርካይቭ ባለሙያ አቶ አሊ ጌታሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የባህል ማዕከላቱ ከአካባቢው ማህበረሰብና የባህል ተቋማት ጋር በመሆን ባህላዊና ታሪካዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ወደ ባህል ማዕከሉ በማምጣት ተማሪዎች እንዲያውቋቸው ብቻ ሳይሆን ለጥናትና ምርምር ሥራዎች ግብአት እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል።
ይህ ካልሆነም ተማሪዎች ቦታው ድረስ ሄደው እንዲመለከቷቸውና ስለባህላቸው፣ ታሪካቸውና አጠቃላይ አገራቸው ምንነትና ስለእራሳቸው ማንነት እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል። የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልም በዞኑ ከሚገኙ 27 ወረዳዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ይህንን እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የጋራ አኩሪ ታሪካቸውን እንዲያውቁት፣ የጋራ ማንነታቸውን በአግባቡ እንዲረዱት፤ አካዳሚያዊ እውቀታቸውንም እንዲያጎለብቱ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አሊ፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥም ተማሪዎች ገና ሲገቡ ከአቀባበል ጀምሮ እስኪመረቁ ድረስ ተማሪዎች የሥነ-ጽሑፍ ውድድርና የንባብ፣ የሙዚቃ እና ሌሎች መርሀ ግብሮችን እንደሚያዘጋጁና እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
የመርሀ ግብሮቹ መዘጋጀትም ተማሪዎች በተለያዩ መስኮች በፍላጎታቸው እንዲሳተፉና ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከማስቻሉም በላይ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፤ እንዲግባቡ፣ የሰለጠነ ውይይት እንዲለማመዱ፤ አገራቸውን በትክክል እንዲገነዘቡ፤ አንዳቸው ያንዳቸውን ባህል እንዲያውቁና እንዲከባበሩ ያደርጋቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲ ማለት ትንሿ ኢትዮጵያ ማለት ነው የሚሉት አቶ አሊ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልም ይህንኑ መነሻ አድርጎ እንደሚሰራ፤ ይህም አንድነትን ከማጠናከርና በተቋሙ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ አኳያ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን የሚናገሩት አቶ አሊ ይህንን አላማ ለማሳካትም የተለያዩ ምሁራንን፣ አርቲስቶችንና ታዋቂ ሰዎችን ከአዲስ አበባ ድረስ በማስመጣት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እንደሚያደርጉና ይህም በተማሪዎች እንደተወደደ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ ግጭቶችን በተመለከተም «እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን አንድነት ነው። አንድ ላይ ስንበላ፣ አንድ ላይ ስንጠጣ፣ አብረን ስንሄድ፣ በአገራችን ጉዳይ በአንድ ላይ ስንሰለፍ ነው እንጂ ስንጋጭና እርስ በእርስ ስንጣላ አያምርብንም።
ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ስለሚበዙ እነሱን ነው ማሰብ ያለብን። በመሆኑም ግጭቱ አይበጅምና ሰላም እንዲሰፍን ተማሪውም ሆነ የዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበረሰብ አባላት በዚሁ መንገድ ቢያስቡበት ጥሩ ነው።» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ግርማ መንግሥቴ