አዲስ አበባ፡- የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጸደቀው አዋጅ የዜጎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት እንደማይገድብ በተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።
የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትናንት የጸደቀውን አዋጅ በተመለከተ የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጎዴቦ እንደገለጹት፤ ረቂቅ አዋጁ ከሰብዓዊ መብትና ከሌሎች ሕጎች ጋር ተገናዝቦ የተዘጋጀ በመሆኑ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ እንጂ የሚገድብ አይደለም፡፡
አዋጁ በጸደቀበት ወቅት አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ጥያቄ ማንኛውም ዜጋ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ክፍል ሁለት አንቀጽ 29 ያለምንም ጣልቃገብነት በመረጠው የማሰራጫ ዘዴ ሃሳብን በነፃነት ያለገደብ የመግለጽ፣ የመቀበልና የማሰራጨት መብት ተሰጥቶታል።
በዚሁ አንቀጽ ቁጥር ስድስትና ሰባት የጦርነት ቅስቀሳዎችንና ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን የተከለከሉ እንደሆነና በሕግም ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ተቀምጧል።
ለዚህም የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 607 እስከ 619 ሃይማኖትን፣ዘርንና ፖለቲካን መሠረት ያደረገ በሀሰት የሚያጥላላ የሚያነሳሳ እንዲሁም ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ማናቸውም ጸያፍና የአማኝነት ስሜትን የሚነካ ድርጊት የፈጸመ ሰው እንደሚቀጣ የተቀመጠ በመሆኑ በዚህ መከላከል ይቻላል።
ጉዳዩ መታየት ካለበትም የመንግሥት አካላትን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና ሚዲያዎችን እንጂ ሌሎች ዜጎችን የሚመለከት መሆን የለበትም። ከዚህ አኳያ ይህንን አዋጅ ማጽደቅ ሃሳብን በነፃነት መግለጽን የሚገድብ በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝንና የዜጎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የሚገድብም ይሆናል ብለዋል።
አቶ አበበ ጎዴቦ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው እየተፈናቀለ ላለው ዜጋና እየፈረሱ ላሉት የእምነት ተቋማት ነው። በአሁኑ ወቅት በሀሰት መረጃ በመነሳሳት ከኢትዮጵያዊነት ባህልና እሴት ውጪ የሆኑ በርካታ ነገሮች እየተፈጸሙ ናቸው።
አዋጁ ሃሳብን የመግለጽን መብት ከኃላፊነት ጋር የሚያስኬድ በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲዘጋጅ አሁን ያለው ቴክኖሎጂና ነባራዊ ሁኔታ አልነበረም። የሀሰት ወሬዎች በአጭር ጊዜ በርካታ ቦታዎች ስለሚደርሱ ኢትዮጵያን በአሁኑ ወቅት ተጋላጭ አድርጓታል ብለዋል።
አዋጁ ሲዘጋጅ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውንም ሃሳብ መነሻ በማድረግ ማሻሻያ ተደርጓል። በልዩ ሁኔታ የሃይማኖት ስብከትን የፓርላማ ንግግርንና ምርምሮችን በልዩ ሁኔታ በመያዙ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት አይገድብም።
ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውና እንደ ሕገ መንግሥቱ አካል የምታያቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም የሚደግፉት ጭምር ነው። በተጨማሪ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ፍጹማዊ መብት ሳይሆን ገደብ ሊጣልባቸው ከሚችሉ መብቶች መካከል የሚመደብ ነው።
በመሆኑም ሰብአዊ መብትን የሚነካ ባለመሆኑና ከሌሎች ሕጎች ጋር ተገናዝቦ የተዘጋጀ በመሆኑ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ እንጂ የሚገድብ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 በመሆን በ23 ተቃውሞና በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ