አዲስ አበባ አማኑኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የምትኖረው ወይዘሮ ፋናዬ አስራት ሰሞኑን 50 ኪሎ ጤፍ አንድ ሺ ሰባት መቶ ሰማንያ ብር ከወፍጮ ቤት መግዛቷን ትናገራለች። ይሁን እንጂ ከአንድ ወር በፊት ተመሳሳዩን ምርት አንድ ሺ 530 ብር መግዛቷን ታስታውሳለች። ምክንያቱን ስትጠይቅ ‹‹መኪና ወደ አዲስ አበባ አይገባም›› የሚል ምላሽ እንደሰጧት አስታውቃለች። ‹‹ዋጋው መወደዱ አሳስቦኛል፤ በዚህ ከቀጠለም አቅሜን ይፈታተናል፤›› ብላለች።
ከዚህ የገበያ ቦታ ከስምንት አመት በፊት የእህል ወፍጮ ቤት ከፍተው ሥራ የጀመሩት አቶ ተፈራ እጅጉ አንደኛ ደረጃ የተባለውን ጤፍ በኩንታል ስምንት መቶ ብር፤ አነስተኛውን በኩንታል እስከ አራት መቶ ብር ይሸጡ እንደነበር ይገልጻሉ። በአሁኑ ጊዜ አንደኛው በኩንታል ሶስት ሺ ሰባት መቶ ብር፣አነስተኛውን ደግሞ በሶስት ሺ ብር በመሸጥ ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል።
አቶ ተፈራ እጅጉ ከአቅራቢ ደንበኞቻቸው ተረክበው ለሸማቹ የሚያቀርቧቸው የጤፍ አይነቶች የአዳ፣የበቾ፣የአቦቴ እና የጎጃም ናቸው። በአሁኑ ጊዜም የአቦቴ ጤፍ ነጭ በመሆኑ ዋጋው ሶስት ሺ ሰባት መቶ ብር ነው። የተቀሩት ጠቆር ያሉ በመሆናቸው ሶስት ሺ ብር ይሸጣሉ። ዋጋው በመወደዱ አንደኛ ደረጃ ጤፍ ይገዟቸው የነበሩ ደንበኞች የመጨረሻውን ዋጋ መምረጥ ጀምረዋል። አንዳንዶችም የሚገዙትን የኪሎ መጠን ቀንሰዋል። አቅም አጥተው ዱቤ የሚወስዱም አሉ።
ጤፍ ከሚያቀርቡላቸው ደንበኞቻቸው ግዥ የሚዋዋሉት በስልክ ስለሆነ አርሶአደሩ የሚያቀርብበትን ዋጋ አያውቁትም። በሚያደርጉት የስልክ ግንኙነት በዋጋ ካልተስማሙ አቅርቦቱ ስለማይኖር ገበያው በአቅራቢ ደንበኛቻቸው ይወሰናል። የመደራደር አቅምም የላቸውም። ከየአይነቱ በሳምንት 30 ኩንታል ይረከባሉ። በዚህ የተገደቡት በቂ አቅርቦት ባለመኖሩ ነው።
አቶ ኢሳያስ ለማ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ናቸው። የምርት አቅርቦት ማነስ በምክንያትነት መነሳቱን አይስማሙም። የአምስት አመት መረጃ የሚያሳየው የሚታረሰው የጤፍ መሬት ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ወደ ሶስት ነጥብ አንድ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ብሏል።
በመቶኛ ሲሰላም በአራት ነጥብ አምስት አድጓል ይላሉ። በምርት ደረጃም የዛሬ አምስት አመት የነበረው አጠቃላይ የጤፍ ምርት 44 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ወደ 58 ነጥብ አንድ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። ምርታማነቱም በሄክታር ይገኝ ከነበረው ከ16 ወደ 18 ኩንታል አድጓል።
‹አንድ ሰው አመታዊ የእህል ፍጆታው በአማካይ አንድ ነጥብ አምስት ኩንታል ነው። በዚህ ስሌት አንድ ሰው ሲወለድ አንድ ነጥብ አምስት ኩንታል ፍላጎት ይኖረዋል፡፡› የሚሉት አቶ ኢሳያስ፤ ከዚህ አንጻር የምርትና ፍላጎት አለመጣጣም ጥያቄ ቢነሳም አሁን የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ምክንያታዊ ነው ብለው አያምኑም።
ምርት ጨምሮ አደጋዎችም ባላጋጠሙበት ሁኔታ ይልቁንም የሚቆጣጠር አካል የለም ከሚል በሸማቹና በነጋዴው መካከል ባሉ ተዋናዮች የተፈጠረ የዋጋ ንረት አድርገው ይወስዱታል። ይህ ጤነኛ የሆነ የገበያ ሥርአት እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉም ይከራከራሉ።
በአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የኢንስፔክሽንና ሪጉራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ጥላዬ የችግሩን አሳሳቢነት ሲገልፁ የምግብ ዋጋ ንረት ከ2011 ዓ.ም ግንቦት ወር ወዲህ ነው የጀመረው። ቢሮው ከመጠባበቂያ ምግብ ክምችት ያገኘውን 90ሺ ኩንታል ለከተማው ነዋሪ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን አረጋግቷል። አሁን ምርት የገባበት ወቅትም ቢሆን ችግሩ አልተቀረፈም።
ገበያውና አምራቹ ጋር ያለው ዋጋ አለመራራቁን በምክንያት በማንሳት አቅርቦቱ ከምንጩ መፈተሽ አለበት ይላሉ። ከአርሶአደር የአካባቢ ነጋዴ፣ከዛ ከፍ ያለ ነጋዴ፣ ከእርሱ ደግሞ የከተማ ነጋዴ፣ ደላላ፣ ወፍጮ ቤት እያለ ሰንሰለቱ ይረዝማል። የንግድ ሱቆች ኪራይ ዋጋ፣ የኤሌክትሪክና የውሃ ታሪፍ መጨመር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለአጠቃላይ የምግብ ዋጋ ንረት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በክትትልና ቁጥጥር ስራ ተለይቷል፡፡
አቶ ኢሳያስ ጤነኛ የገበያ ሥርአት ስለአለመኖሩ ቢገልፁም አቶ ሀብታሙ ግን ‹‹ነጻ ገበያ በመሆኑ መንግሥት የዋጋ ትመና ውስጥ አይገባም። ለዋጋ ንረት ምክንያት የሆኑትን ግን ይለያል። የምርት ማነስ፣ ህገወጥነት፣ በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ማነቆዎች ካሉ ለይቶ መፍትሄ ያስቀምጣል።
የምርት አቅርቦት ችግር ተጠቃሽ ነው።›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶክተር ዳዊት ሀየሶ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰርና የአስተዳደርና የተማ ሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬ ዚዳንት በሰጡት አስተያየት የሚስተ ዋለው የዋጋ ንረት በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል የሚፈጠር ነው ሲሉ የአቶ ሀብታሙን ሀሳብ ያጠናክራሉ።
‹‹ለምሳሌ ግብርና ሚኒስቴር አምና አንድ መቶ ኩንታል ቢያመርት ዘንድሮ ደግሞ አስር ኩንታል ጭማሪ ቢያመርት ለእርሱ የቁጥር እድገት ነው። ፍላጎት ግን ከመቶ አስር ላይሆን ይችላል። የተመረተው ምርት ገበያው ከሚፈልገው በላይ ሆኖ በዋጋ መረጋጋቱ ላይ ሚና ሲኖረው ነው ምርት ጨምሯል የሚባለው›› ሲሉ ይከራከራሉ።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ ግብአትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ከዚህ ቀደም ከሚታረሰው መሬት በላይ የእርሻ ሥራ አለመጨመር፣በአጠቃላይ በዘርፉ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ አለመከናወኑ የራሱ ድርሻ አለው። የማምረቻ፣ የማዳበሪያ የሰው ጉልበት እንዲሁም የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሜነት መስፋፋትም በዋጋ ንረቱ ጫና ፈጥረዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ የዋጋ ንረቱ አሁንም ማቆሚያ የለውም ይላሉ። ለመንስኤው የሚመጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍን ቀዳሚ መፍትሄ አድርገው ይወስዳሉ። ሌላው አርሶአደሩን መደጎም ነው። በዝቅተኛ ወጪ ሲያመርት በዝቅተኛ ዋጋ ያቀርባል። እንደ ኤዥያ ፣ላቲን አሜሪካ አውሮፓ የመሳሰሉ ሀገራት አርሶአደሮቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚደጉሙ ለአብነት ያነሳሉ። ለገበያው እንቅፋት የሆኑትን እንደ መጓጓዣ፣መንገድና የአካባቢ ሰላም ስጋቶች ላይም መስራት ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/20122
ለምለም መንግሥቱ