አዲስ አበባ፡- የምርጫ ሜዳውን የሰፋ ከማድረግ አንጻር የብልጽግና ፓርቲ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ ገለጹ፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የመዝጊያ ስነ ስርዓት ትናንት ተካሂዷል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ምርጫው ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ብልጽግና ፓርቲ ከሁሉም በላይ በኃላፊነት እየሰራ ነው፡፡ ፓርቲው ተወዳዳሪ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የመወዳደሪያ ሜዳው የሰፋና ሁሉንም የሚያሳትፍ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
ገዢው ፓርቲ የምርጫ ቦርድን በአደረጃጀት፣ በቁሳቁስና በበጀት አቅም የማጎልበት ሥራ እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ አወሉ፤ ፓርቲው በአሁኑ ወቅት አገርን እያስተዳደረ ያለ በመሆኑ የአገራዊ ኃላፊነት ግዴታ እየተወጣ መሆኑንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አገልግሎት ላይ ሰፊ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የምርጫ ጨዋታውንና ሜዳውን የሰፋ ከማድረግ አንጻር በርካታ ሥራዎች ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ድርሻውን መወጣቱንም አመላክተዋል፡፡
አቶ አወሉ አክለውም ከምርጫ ሰሌዳ ጊዜ ውጭ እየተደረጉ ያሉ ነገሮች መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ይህንንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ስርዓት ማስያዝና፤ ፓርቲዎች ዓላማቸውንና ፕሮግራማቸውን ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለደጋፊዎቻቸው በትክክል የሚያደርሱበትን ሂደት ታሳቢ ያደረገ ሥራም ይሰራል ብለዋል፡፡ በዚህም ምርጫው ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲው ውይይት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ለ17 ቀናት የቆየው የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ስልጠና ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ አገራዊ ለውጡና እመርታው ላይ ሰፊ ውይይት መካሄዱን፤ በለውጡ የታዩ ተግዳሮቶች፣ ለውጡን ለማስቀጠል የነበሩ አካሄዶች እና በቀጣይ ሊደረጉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አመራሩ ስልጠና መውሰዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/20122
አዲሱ ገረመው