አዲስ አበባ፡- ‹‹ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የፌዴራል ስርዓት አልነበረም፤ የሚለውም ሆነ ከለውጡ በኋላ አሃዳዊ ስርዓት እየተገነባ ነው የሚሉት ሃሳቦች ውሸት ናቸው›› ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር እና የዩኒቨርሲቲው የውጭ ጉዳይ ትብብርና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ አጭሶ ተናገሩ፡፡
ዶክተር ደመቀ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ከለውጡ በፊት ፌዴራል ስርዓት አልነበረም የሚለው ሃሳብ የተሳሳተ ነው፡፡ ከነክፍተቶቹም ቢሆን ከለውጡ በፊትም በኢትዮጵያ ውስጥ የፌዴራል ስርዓት ነበር፡፡
ሆኖም ክልሎች በህገ መንግሥቱ የተደነገገውን መብት ያለመጠቀም ችግርን ጨምሮ የተለያዩ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ክፍተቶች የፌዴራል ስርዓት አልነበረም ከሚል ድምዳሜ የሚያደርስ አይደለም፡፡
ከለውጡ በፊት በፌዴራል ስርዓቱ ላይ የነበሩትን ክፍተቶች ነቅሶ በማውጣት እንዲስተካከሉ ከማድረግ ይልቅ ጭራሽ አልነበረም ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን ዶክተሩ አንስተዋል፡፡
‹‹ከለውጡ በኋላም በፌዴራል ስርዓቱ መዋቅር ላይ ምንም ዓይነት የተደረገ ለውጥ የለም፡፡ የነበረው ፌዴራሊዝም ነው እንዲቀጥል የተደረገው›› የሚሉት ዶክተር ደመቀ፤ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ከመካሄዱ ባሻገር ምንም የተደረገ ለውጥ የለም ብለዋል፡፡ አንዳች ለውጥ ባልተደረገበት የፌዴራል ስርዓቱ ተናግቷል፤ አሃዳዊ ስርዓት እየተገነባ ነው የሚለው ውንጀላ ውሃ የማይቋጥር ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡ ‹‹የፌዴራል ስርዓቱ እየፈረሰ ነው የሚሉ አካላት ታሪክ እና አመክንዮ ላይ ተመስርተው ማብራሪያ የሚሰጥ ማብራሪያ ያለ አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ደመቀ ማብራሪያ፤ ከለውጡ በኋላ ጽንፍ የረገጠ አሃዳዊነትንና ጽንፍ የረገጠ ብሄርተኝነትን ወደ መሃል በማምጣት ህብረብሄራዊ፤ ሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሁሉም ሰው እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት ለመገንባት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
ከለውጡ በፊት የፌዴራል ስርዓት ጭራሽ አልነበረም የሚሉት እንዲሁም ከለውጡ በኋላ የፌዴራል ስርዓቱ እየፈረሰ ነው የሚሉት ሁለቱም ሃሳቦች ሁለት ጽንፍ ላይ ቆመው የቀሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ሁለቱም ጠቃሚ አይደሉም ሲሉም አክለዋል፡፡ ለውጡን የሚመሩ አካላት በሁለቱም አቅጣጫዎች በሚሰነዘሩ አስተሳሰቦች ሳይደናገጡ የተጀመረውን ህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓት የማጠናከር ሥራውን ሊቀጥሉ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
የፌዴራል ስርዓት በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሚገነባ ሳይሆን በብዙ ዓመታት ውስጥም ተገንብቶ ላያልቅ ይችላል የሚሉት ዶክተር ደመቀ፤ ፌዴራሊዝምም ልክ እንደ ዴሞክራሲ ሂደት በመሆኑ አንዴ ተገንብቶ የሚያልቅ አይደለም ብለዋል፡፡ ስርዓቱ ከተዘረጋ በኋላ ሁሉም ህብረተሰብ የግንባታ ሚና የሚጫወትበት ስርዓት እንደመሆኑ ሁሉም በስርዓቱ ግንባታ ውስጥ የራሱን ሚና መጫወት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/20122
መላኩ ኤሮሴ