- ወደ ኬንያ የሚሻገሩ አህዮችን በመቆጣጠር ተጠምዷል
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከወጪና ገቢ ህገ ወጥ ንግድ /ኮንትሮባንድ / 134 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መያዙን የሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡ በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የሚሻገሩትን አህዮች በመቆጣጠር መጠመዱንም ገለጸ፡፡
የሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጫንያለው ፋጂ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ ከነበሩ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ምርቶች 134 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት በቁጥጥር ስር ያዋለው ከሞያሌ እስከ ዶሎ ስምንት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በሚደርስ ቦታ በተደረገ ክትትል ነው፡፡
የኬንያ ወደብን ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ፣ብትን ጨርቆችና ልባሾች፣ መድሃኒቶች፣ ሞተር ሳይክሎች፣ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉት የኮንትሮባንድ ዓይነቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ለማውጣት የሚሞክሩትም አብዛኞቹ የግብርና ውጤቶች ሲሆኑ ከእነዚህም እንደ ቦለቄና ማሾ የመሳሰሉ የቅባት እህሎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ገልጸዋል።
እንስሳትን በተመለከተ እንደ ወይፈን ፣ግመል ፍየልና በግን የመሳሰሉት እንደ የሀገራቱ የዋጋ ሁኔታ አንዳንዴ ከኬንያ ወደ አገር ውስጥ የማስገባትና አንዳንዴም ከሀገር ውስጥ ወደ ኬንያ የማስወጣት ሙከራ እንዳለ አቶ ጫንያለው ገልጸዋል። በአጠቃላይ በስድስት ወር አፈጻጸማቸውም ከወጪና ገቢ ህገ ወጥ ንግድ 134 ሚሊየን ውስጥ 22 ሚሊየን የሚገመተው ከወጪ ህገወጥ ንግድ በተለይም ከቅባት እህሎች የተገኘ መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ባለፉት ስድስት ወራት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የሚሸጋገሩ አህዮች ፍሰት ከፍተኛ እንደሆነ ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፤ በኬንያ የአህያ ስጋን ኤክስፖርት የሚያደርጉ ፋብሪካዎች መኖራቸው አህዮችን ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚያሸጋግሩ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ቁጥር ተባብሶ መቆየቱን አመልክተዋል። በዚህም የሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ከፍተኛ የመከላከል ሥራ እንደሠራ ተናግረዋል።
ቅርንጫፍ ጣቢያው የሚገኝበት ስፍራ በርሃማና የእንስሳት መኖ የማይገኝበት በመሆኑ የሚያዙ አህዮችን ማቆየት እንደማይቻል ጠቅሰዋል። ይሁንና ጥብቅ ክትትል በማድረግ ከተፈቀደላቸው ቀጣና ርቀው በመሄድ ጭምር በህገ ወጥ ንግድ ሊወጡ የነበሩ አህዮችን እየተቆጣጠሩ ለክልሎች መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ከኬላዎች ርቀው በጫካ ውስጥ አህዮችን በእግራቸው እያቆራረጡ በመንዳት ለማሻገር የሚሞክሩ ህገ ወጥ አካላት መኖራቸውን አቶ ጫንያለው ገልጸዋል። በተለይም በቦረና ዞን በሚኦ ወረዳ ሶሎሎ በሚባል አካባቢ ፍሰቱ ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው፤ በተደረገ ክትትል በርካታ አህዮች ወደ ውጭ እንዳይወጡ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ጉዳዩን ለንግድ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውንና በቅንጅት በመሥራት ፍሰቱን ለመቀነስ መቻሉንም አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት ህገ ወጥ ንግድ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያሽመደምድና የብዙኋኑን ተጠቃሚነት የሚጎዳ በመሆኑ ጉዳዩን የአንድ ተቋም ኃላፊነት አድርጎ ከመመልከት ይልቅ እያንዳንዱ ዜጋ ክትትልና ጥቆማ በማድረግ መተባበር እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/20122
ኢያሱ መሰለ