ጉዟችን ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ደሎመና ወረዳ ነው። ከአዲስ አበባ ከተማ 400 ኪሎ ሜትር። ከባሌ ጎባ ደሎመና ድረስ ያለው 120 ኪሎ ሜትር ግን ‹መንገድ ያደርሳል መንገድ ይመልሳል› እንደሚባለው ዓይነት አይደለም። ለመኪና አስቸጋሪና ምቾት የሚነሳ ነበር። በወረዳው ከመኪና ይልቅ ሞተር ሳይክሎች ለአይን ሞልተው ይታያሉ። ነዋሪው የተለያየ የልማት ጥያቄ ቢኖረውም የመንገድ ልማት ጥያቄው ግን የጎላ ድርሻ አለው።
ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ለአገልግሎት ያበቃው ስድስት መቶ ሄክታር የሚሸፍነው የመስኖ ልማት ምረቃ እና በፌዴራል መንግሥት የሚገነባው የ11ሺ40 ሄክታር የመስኖ ልማት ይፋዊ ሥነ-ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሥፍራው መገኘታቸው ለነዋሪው የልማት ጥያቄ ተስፋ ሰጥቷል።
የዞኑ ወረዳ ደሎ መና ልማት እየጎበኛት ነው። በኦሮሚያ ክልል ወደ ስድስት መቶ ሄክታር የሚሸፍን የመስኖ ልማት ሥራ ከሦስት ወር በፊት ተጠናቅቆ አርሶ አደሩ በማሳው ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት ጀምሯል።
ምርቱን ወደ ገበያ የሚያቀርበው ግን በሞተርሳይክል ነው። ይሄ ደግሞ ለገበያ ሰንሰለቱ የልብ አያደርስም። ልማቱ ጅምር ቢሆንም ከወዲሁ ካልታሰበበት አካባቢውን በልማት ለማሳደግና የነዋሪውን ኑሮ ለመቀየር የሚደረገው ጥረት ከመንገድ እንዳይቀር ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ልማትና ሰላም ፈላጊ እንደሆኑም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
በደሎ መና በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ራዲያ ባቲ ቀደም ሲል የጎበኛቸው መሪ ባለመኖሩ ‹‹ተረስተናል›› የሚል ስሜት ስለነበራቸው መሪዎቹ በመገኘታቸው ተደስተዋል። መምጣታቸው ብቻውን በቂ እንዳልሆነና ቃል የገቡትንና የጀመሩትን ልማት አጠናክረው ለውጤት እንዲያበቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሀገር ሰላም ካልሆነ የመንገድ ሥራም ሆነ ልማት እንደማይታሰብ የሚገልጹት ወይዘሮ ራዲያ፤ መንግሥት የህግ የበላይነት እንዲከበር መሥራት እንዳለበትና ህዝብም ለህግ ተገዥ ሆኖ ለልማት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲነሳ ጠይቀዋል።
የወይዘሮ ራዲያን ሃሳብ የሚጋሩት በደሎ መና ወረዳ መልካአማና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሃሊማ መንግሥት መኖሩን ማየት በራሱ ትልቅ ተስፋ እንደሆነና ከዚህ በኋላም ነዋሪው የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለልማት ይነሳሳል ብለዋል። ‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመንገድ፣የውሃና ሌሎችም የልማት ጥያቄዎቻችንን ይዘው ተመልሰዋል። መልስ እንደሚሰጡን ተስፋ እናደርጋለን› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
በአካባቢው የተጀመረው የአትክልት ልማት ተስፋ እንዳሳደረባቸውና ልማቱን የጀመሩ አርሶአደሮች መሬታቸውን በትራክተር አርሰው እንዲያለሙ በነፃ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን መስማታቸው ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ ብዙዎችንም ለልማት እያነሳሳ እንደሆነ አመልክተዋል። ልማቱ አትክልት በአቅራቢያቸው ለማግኘት፣ የህብረተሰቡ የአመጋገብ ባህል እንዲለወጥ መርዳቱንም ገልጸዋል።
የመልካም አስተዳደር ጉዳይ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል የሚሉት ወይዘሮ ሃሊማ ከለውጡ በፊት የነበሩ አንዳንድ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች በኃላፊነት ላይ መኖራቸውንና ያደርሱት የነበረው የመልካም አስተዳደር በደል አለመቀረፉን ያስረዳሉ። መንግሥት በአካባቢው ልማት እንደጀመረው ሁሉ በመልካም አስተዳደሩ ላይም ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበትና መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ካደረገ ህዝቡ አስቸጋሪዎችን ለይቶ ለመስጠትም ሆነ ሰላም ለማረጋገጥ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከብት በማርባት የሚተዳደሩት ሁሴን አደም አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ ለእርሻም ሆነ ከብት ለማርባት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ፣ በመንገድ ችግር የተሻለ ገበያና ለከብቶቻቸው መድኃኒት ለማግኘት ፈተና እንደሆነባቸው ያስታውሳሉ። የከብት አርቢ ልጆች የትምህርት ዕድልም እንደሌላቸውና የአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሰፊ እንደሆኑ ያስረዳሉ።
የተጀመረው ልማት ተስፋፍቶ የከብቶቻቸው የዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ጨምሮ ትርፋማ የሚሆኑበትን ጊዜ የሚናፍቁት አቶ ሁሴን የመንግሥት ትኩረት ከቀጠለ እድገት እንደሚኖር ተስፋ አድርገዋል። ከእርሳቸው የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግም ዝግጁ ናቸው።
በመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አሊ ዳውድ በከብት እርባታ የሚታወቀውን አካባቢ የእርሻ ሥራን በማጠናከር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መጀመሩ አስደስቷቸዋል። የከተማውም ሆነ የገጠሩ ነዋሪ ኑሮ ይለወጣል ብለው ያስባሉ። የተጀመረው መነቃቃት በጠንካራ አመራር መታገዝ እንዳለበት ገልጸዋል። የአካባቢያቸው ነዋሪ ሰላም ፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ቢሮ ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ የመስኖ ልማቱ ከድህነት ለመውጣትና ተፈጥሮን በመጠበቅ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣውን አደጋ የመከላከል ሁለት ዓላማዎች ይዞ የሚከናወን መሆኑን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት በክልሉ አቅም ለአገልግሎት የበቃው 600 ሄክታር የሚያለማው የወልመል መስኖ ልማት አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ከሚጠቀመው በተጨማሪ የተደራጁ 170 ወጣቶች ባልተያዘ መሬት ላይ እንዲያለሙ ተደርጓል። የክልሉ ህዝብ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የተጠናከረ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ልማትና ሰላም የማስተሳሰር ሥራ መጠናከር እንዳለበትም የሁሉም መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/20122
ለምለም መንግሥቱ