አዲስ አበባ፡- ከህንድ ሎክማኒያ ሆስፒታል በመጣው የህክምና ቡድን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ውስጥ እየተሰጠ ያለው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ዘመቻ የእውቀት ሽግግርን እንደሚያጠናክር ተጠ ቆመ፡፡
የህክምና ቡድኑ እየሰጠ ያለውን ይህንኑ የቀዶ ህክምና ዘመቻ አገልግሎት በተመለከተ ትናንት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት የሆስፒታሉ የሜዲካል አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ሊያ ተፈራ እንደገለፁት፤ ከአስራ አራት በላይ የሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎችን የያዘው ቡድኑ የአንጀት፣ የሽንት መተላለፊያ ቱቦና የማህፀን ቀዶ ህክምና አገልግሎቶችን በነፃ እየሰጠ ይገኛል፡፡
ቡድኑ እያደረገ ያለው የቀዶ ህክምና ዘመቻ አገልግሎት ሆድ ሙሉ በሙሉ ሳይከፈት የተለያዩ መሳሪያዎችን በመጠቀምና ታካሚዎችም በቶሎ አገግመው ለመውጣት በሚያመቻቸው መንገድ በመሆኑ ከእስካሁኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ምክትል ፕሮቮስቷ ጠቅሰዋል፡፡
በዘመቻው ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ከህክምና ቡድኑ ጋር አብረው የመስራት እድል እንደገጠማቸው ገልፀው፤ ይህም ወደ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች የሚደረገውን የእውቀት ሽግግር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ጠቁመዋል፡፡
እንዲህ አይነቱ የቀዶ ህክምና ዘመቻ በነፃ የሚሰጥ ከመሆኑ አኳያም በተለይ አገልግሎቱን ማግኘት ለማይችሉ ታካሚዎች ከቤታቸውና ከቤተሰቦቻቸው ሳይርቁ ለመታከም ያስቻላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገውም ገልፀዋል፡፡
ከህመሞቹና ከሚሰሩት የቀዶ ህክምና አይነቶች አንፃር እስካሁን በዘመቻው የተከናወነው የቀዶ ህክምና ምን ያህል ወጪ እንዳስወጣ በትክክል ማስቀመጥ ባይቻልም ታካሚው ወደ ህንድ ሀገር ሄዶ አገልግሎቱን ቢያገኝ ከሶስት እስከ አምስት ሺ የአሜሪካን ዶላር ሊያስወጣው ይችል እንደነበረም ምክትል ፕሮቮስቷ አስታውቀዋል፡፡
የህክምና ቡድኑ እስከ መጪው አርብ ድረስ የቀዶ ህክምና አገልግሎቱን በመስጠት ከስልሳ እስከ ሰባ ለሚሆኑ ታካሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ህክምናውን የሰጠ ሲሆን እስካሁን ለሶስት ቀናት በሰጠው አገልግሎት ሰላሳ የሚሆኑ ታካሚዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/20122
አስናቀ ፀጋዬ