አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት መሐመድ ቡሃሪ በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ባካሄዱት ውይይት የምዕራብና የምስራቅ አፍሪካን ቀጣናዎች ለማስተሳሰር እንደሚሠሩ መግለፃቸው ተጠቆመ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የሁለቱን አገራት መሪዎች ውይይት አስመልክተው ትላንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች ያካሄዱት ውይይት በኢኮኖሚውም ሆነ ብዝኃነትን በማጠናከር ረገድ በሁለቱም አገራት የተጀመሩ ሥራዎች አፍሪካ በቀል ተሞክሮዎች ስለሆኑ መማማርና ማደግ እንደሚቻል ትምህርት የተወሰደበት ነው፡፡ በሁሉም ዘርፎች ጠንካራ ትብብር በማድረግ የምዕራብና የምስራቅ የአፍሪካ ቀጣናዎችን ለማስተሳሰር እንደሚሠሩ ሁለቱ መሪዎቹ መክረዋል፡፡
ናይጄሪያ እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃነትን የምታስተናግድ አገር እንደመሆኗ የፌዴራል ሥርዓትን በማጠንከር ረገድ ውይይቱ ሰፊ ተሞክሮዎች ይወሰድበታል ያሉት አቶ ንጉሱ፤ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በሁለቱም አገራት ሰፊ ልምድ መኖሩን፤ ሁለቱ አገራት የጠነከረ ትስስር በመፍጠር ውይይቱ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ንጉሱ ገለፃ፤ አገራቱ የሚጋሯቸው ተመሳሳይ ነገሮች ያሏቸው ሲሆን፤ የጋራ ጥቅሞች ላይ ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ልምድ መለዋወጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ሁለቱም አገራት በፌዴራል ሥርዓት የሚተዳደሩ ስለሆነ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ልምድ መቅሰም ለመማማር የሚያግዝ ነው፡፡ ለዚህም ከፕሬዚዳንቱ ጋር የመጡት ልዑካን ቡድኖች ከማዕከላዊ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የክልል አመራሮችና የሴኔት አባላት መሆናቸው የጠንካራ ትብብሩ ማሳያ ናቸው፡፡
አቶ ንጉሱ ሁለቱ አገራት በሠላም ዙሪያ በጋራ መሥራትና የዲፕሎማት ፓስፖርት ከቪዛ ነፃ እንቅስቃሴ እንዲኖር ስምምነት ማድረጋቸውን፤ ተናጠል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩም መምከራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለወጣቶች የትምህርት፣ የሥራና የተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ በመፍጠር ረገድም ሰፊ ትምህርቶች የተወሰዱበት ውይይት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ የናይጄሪያ ባለ ሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች መስፋት እንዳለባቸው መወያየታቸውን አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ንጉሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዚዳንቱ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በማህበራዊ ዘርፍና በቱሪዝም መስክ የዳበረ ግንኙነት መፍጠር እንዳለባቸው መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡ በእህል ሰብል ራስን በመቻል ረገድም ናይጄሪያ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ከዚህ መማር እንደምትችል ትብብራቸው ከሁለትዮሽ አልፎ ምዕራቡንና ምስራቁን የአፍሪካ ክፍል ማስተሳሰር እንደሚችል መወያታቸውን ተናግረዋል፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛችና ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆኗን በመመስከር በዚህም የራሷን ባህልና ማንነቷን ጠብቃ መቆየቷ ሁልጊዜም ኩራታቸው እንደሆነ መናገራቸውን አቶ ንጉሱ ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012
አዲሱ ገረመው