አዲስ አበባ:- በ33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩ እንግዶች በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ደስተኛ መሆናቸውን ገለፁ።
ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ”ጦርነትና አንድም የጦር መሣሪያ ድምፅ የማይሰማባት አህጉር መፍጠር” በሚል መሪ ሐሳብ በ33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩ አንዳንድ እንግዶችን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ደስተኛ መሆናቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልፀዋል።
ከነዚህ መካከል ለጉባኤው የዜና ሽፋን ለመስጠት ከሞሮኮ የመጣው ጋዜጠኛ ሙሐመድ ፈረሐን እንደገለፀው፤ በዚህ ጉባኤ እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2020 ለተከታታይ ስድስት ዓመታት ታድሟል። በነዚህ ዓመታት አዲስ አበባን ተመላልሶ በተደጋጋሚ እንዳያት ጠቁሞ፤ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን በጣም እንደወደዳት ተናግሯል።
የከተማዋ ሰላምና ደህንነት የተጠበቀ መሆኑን የሚናገረው ጋዜጠኛው፤ ጉባኤው በሚካሄድበት በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እንዲሁም ከአዳራሹ ውጪ በሆቴሎች መስተንግዶና አገልግሎቶች በጣም መደሰቱን ጠቁሞ፤ ህዝቡ እጅግ ቀናና ሰው ወዳድ መሆኑን፤ በነበረው ቆይታ በጣም ደስተኛ እንደነበር ገልጿል።
በከተማዋ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ባለማግኝቱ መረጃዎችን በፍጥነት ለመላላክ እንዳላስቻለው ጋዜጠኛ ፈርሐን ጠቁሞ፤ የእንተርኔት ቴክኖሎጂው ሊሻሻል እንደሚገባ አስተያየቱን ሰጥቷል። በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ምርቶች ወይም ሸቀጦች ዋጋቸው ተመጣጣኝ ቢሆንም ቅሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በጣም ውድ መሆናቸውን የሚናገረው ጋዜጠኛው፤ በሆቴል ላይ ያለው አገልግሎትና መስተንግዶ ጥሩ ቢሆንም የተጋነነ ዋጋ እንደሚጠየቅ ተናግሯል።
በየዓመቱ በጉባኤው አያሌ ሰዎች ይታደማሉ። እነዚህ እንግዶች ከአራቱም ማዕዘን የሚመጡ በመሆናቸው ደርሰው ሲመለሱ በተለያየ አገር አምባሳደር ሆነው አገሪቱን ስለሚያስተዋውቁ ሆቴሎች ትርፋቸውን ከማስቀደማቸው በፊት ለአገር ገፅታ ግንባታ ሲባል እንግዶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያስተናግዱ እንደሚገባ አሳስቧል።
ከደቡብ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የመጣውን ልዑክ በመምራት አህጉር አቀፍ ብሎም ዓለም አቀፍ የዜና ሽፋን ለጉባኤው ለመስጠት የመጣችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ሶፊ መቆይና በበኩሏ፤ <<ህዝቡ እንደተለመደው እንግዳ ተቀባይና ሰው ወዳድ ነው። ባያውቅህም ሞቅ ያለ ሰላምታ ይሰጥሐል። ቋንቋ ባይችል እንኳን በሚችለው ለመርዳት እና ሰላምታ ለመስጠት ወደ ኋላ አይልም። በአጠቃላይ በነበረኝ ቆይታ በተደረገልኝ አቀባበልና መስተንግዶ ተደስቻለሁ>> ብላለች።
በኢሚግሬሽን የተደረገልን ክብካቤ በጣም ጥሩ ቢሆንም ለሥራ ከሚያስፈልጉን መሣሪያዎች ውስጥ ይዘን መግባት የምንችለውና የማንችለው በግልፅ ባለመቀመጡ ለሥራ የሚያስፈልጉንን ዕቃዎች ለማስ ገባት በጣም ከባድ ነበር ያለችው ጋዜጠኛዋ፤ ከዚህ ባሻገር የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኝት በጣም ከባድ እንደሆነባትና በተለይ ከስብሰባ አዳራሹ ወጥቶ ታክሲ እንደልብ ለማግኝት ተቸግራ እንደነበር ገልፃለች።
ከአሁን በፊት በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሲሠራ የነበረው እና በአሁኑ ወቅት በዩኔስኮ እንደሚሠራ የሚናገረው ሚሻዱ ኖማን በበኩሉ፤ ዩኔስኮ ከመግባቱ በፊት በአፍሪካ ሕብረት ለአንድ ዓመት እንደሠራና በጥቅሉ ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ በኢትዮጵያ መቆየቱን ይናገራል።
እዚህ በቆየበት ዓመታት የታዘበውን እንደተናገረው፤ <<ህዝቡ በጣም ደግና ተግባቢ ነው። የህዝቡን እንግዳ ተቀባይነት በጣም ነው የምወደው። በተመሳሳይ የኢትዮጵያውያንን ዋና ምግብ የሆነውን እንጀራና ጥብስ በጣም እወደዋለሁ።
የኔ ተመራጭ ምግብ ነው። እዚህ በቆየሁበት ሦስት ዓመታት እንዳየሁት የህብረተሰቡን ባህል በተለይ ባህላዊ ጭፈራዎችንና ህብረተሰቡ ለሰዎች ያለውን ክብር በጣም ወድጀዋለሁ>> ሲል ገልጿል።
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012
ሶሎሞን በየነ