አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራ መበራከት ለከተማው አስተዳደር ፈተና እየሆነ መምጣቱን ኮሚሽኑ ገለፀ።
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራር በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባካሄደበት ወቅት የኮሚሽኑ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ከፋለ ኮሚሽኑ ቀደም ሲልም ከመሬት ጋር በተያያዘ ወንጀሎችን የመመርመር፣ ጥፋተኞችን ለፍርድ የማቅረብና የመከላከል ሥራዎችንም የሠራ ቢሆንም አሁንም በመሬት ዘርፍ የሚስተዋሉ ሙስና፣ ብልሹ አሠራሮችና ሕገ ወጥ ወረራዎች የከተማዋን ገጽታ እያበላሹና የሕግ የበላይነትን እየተፈታተኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ በአመራር ላይ ያሉ አካላት የመንግሥትን መሬት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባቸው፤ ኮሚሽኑም በተሰጠው ሥልጣን ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን የመከላከል ሃላፊነት እንዳለበት አስረድተው፤ ሙስናና ብልሹ አሠራር፣ የመረጃ አያያዝ ማነስ፣ የግልፅነትና ተጠያቂነት ችግሮች ከሕግ ሥርዓቶች አለመከበር ጋር ተዳምረው ለመሬት ወረራው መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በከተማው ከመሬት ጋር ተያይዞ ሃላፊነት የተሰጣቸው 17 ተቋማት መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ እነዚህ ተቋማት ተናበው የመሥራት ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው፤ በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመንግሥት ጎን መቆም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ዘርጋው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገ የመጣ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እንቅስቃሴ መኖሩን፤ ይህንንም ለማስተካከል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳሉና መሬትን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቆጥሮ የመያዝና በከተማዋ ባሉ 117 ወረዳዎችም አደረጃጀት ተፈጥሮ በቅንጅት እየተሠራ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
አቶ ኤሊያስ በየአካባቢው ለልማት የተቀመጡ ክፍት ቦታዎችንና አረንጓዴ ቦታዎችን በማን አለብኝነት የማጠርና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከሚሠሩ አካላት ጋር ተመሳጥሮ ካርታ የመውሰድ ሙከራዎች እንደታዩ ገልፀው፤ ድርጊቶቹ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጡ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ እንዳለ አስረድተዋል፡፡
አቶ ኤሊያስ የማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ ያሉት ሰፋፊ ክፍት መሬቶች ጥቅም ላይ እስኪውሉ ድረስ በአርሶ አደሩ እጅ ላይ ያሉ መሆናቸውን ተከትሎ ሕገ ወጥ ወረራ እንደሚካሄድባቸው አስታውሰዋል፡፡
በተለይም በንፋስ ስልክ፣ አቃቂ፣ ቦሌ፣ የካ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እንደሚካሄድ፤ ፖሊስ፣ ደንብ ማስከበር፣ ግንባታ ፈቃድ፣ ከመሳሰሉና ከተቋሙ ጋር ትስስር ካላቸው ባለድርሻዎች ጋር በጋራ የመሥራት አቅጣጫ መያዙን ገልፀዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሕገ ወጥ ወረራን አስመልክቶ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግና ግንባታዎች ከመፈፀማቸው በፊት እርምጃዎችን መውሰድ እንደ ሚያስፈልግ ጠቁመው፤ የፍትህ ተቋማት በመሬት ጉዳይ የሚቀርቡ ጉዳዮችን በአግባቡ ተመልክተው ፍትሐዊ ዳኝነት እንዲሰጡና ሕገወጦችን የሚያበረታታ ውሳኔ ከመስጠት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012
ኢያሱ መሰለ