አዲስ አበባ:- ከማዕድንና ነዳጅ ተፈጥሮ ሀብቶች ከሚገኝው ገቢ ውስጥ 50 በመቶው ሀብቱ ለመነጨበት ክልል እንዲውል መወሰኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የመጀመሪያውን መንፈቅ ዓመት የሥራ አፈፃፀም አስመልክቶ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ላይ በሚኒስቴሩ የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ባምላክ አለማየሁ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለውን የማዕድን ሕግ ጉዳዮችን አስመልከተው እንደገለፁት፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቅርቡ በወሰነው መሰረት ከሐምሌ አንድ ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከማዕድንና ነዳጅ ተፈጥሮ ሀብቶች ከሚገኝው ገቢ ውስጥ 50 በመቶው ሀብቱ ለመነጨበት ክልል ልማት እንዲውል ተወስኗል።
ክልሎች ከማዕድንና ነዳጅ ተፈጥሮ ሀብታቸው ማግኝት የሚገባቸውን ጥቅም ምክርቤቱ በቅርቡ የወሰነውን ውሳኔ ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ከማዕድንና ነዳጅ ተፈጥሮ ሀብቶች ከሚገኝው ገቢ ውስጥ 50 በመቶው ማዕድኑ ወይም ነዳጁ ለተገኝበት ክልል፤ ከ50 በመቶው ውስጥ 10 በመቶው ማዕድኑ ወይም ነዳጁ ለተገኝበት ስፍራ ወይም ኩባንያው ፍቃድ ለወሰደበት ወረዳ ይውላል።
ከቀሪው 50 በመቶ ላይ 25 በመቶው ለፌዴራል መንግሥት ገቢ ሲሆን፤ ቀሪው 25 በመቶ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብቱ ላልተገኝባቸው ሌሎች ክልሎች እንዲከፋፈል ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል። በውሳኔው መሰረት ከሐምሌ አንድ ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ውሳኔው ተፈጥሮ ሀብቱ የተገኝበትን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ማህበረሰቡ ከተፈጥሮ ሀብቱ ልጠቀም ይገባኛል ብሎ ለሚያነሳው ጥያቄ መልስ ሰጭ ነው ያሉት አቶ ባምላክ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ህብረተሰቡ ከተፈጥሮ ሀብቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ አልሆንኩም የሚል ቅሬታ በማንሳቱ እንደሜድሮክ ያሉ ግዙፍ የማዕድን ኩባንያዎች ሥራ ያቆሙበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ውሳኔው ማዕድኑ ወይም ነዳጁ የተገኝበትን አካባቢ ማህበረሰብ ብሎም ሰፊውን የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡ ለማዕድንና ነዳጅ ዘርፉ ቀናኢ አመለካከት እንዲኖረው ከማድረጉ ባሻገር በእውቀቱና በጉልበቱ ለዘርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያስችላል። ይህም ዘርፉ አድጎ የውጭ ምንዛሬ በማስገባትና የአገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
55 ነጥብ 77 ሄክታር በማዕድን ሥራ ምክንያት የተጎዱ ቦታዎችን ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ ሽፋን ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ ከአካባቢ ማህበረሰብ ልማት ፈንድ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን ከመድረኩ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012
ሶሎሞን በየነ