. ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
አዲስ አበባ፡- በአፍሪካ ምድር ሰላም እንዲሰፍንና የአህጉሪቱ ብልፅግና እንዲረጋገጥ የሚሰራ እንደሚሆን በ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገለፀ፡፡ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር አስታውቀዋል።
33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ትናንት በአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ‹‹የጦር መሳሪያ ድምፅን ማስቆም›› በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደበት ወቅት፤ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ የሊቀመንበርነት ኃላፊነቱን ተረክበው ህብረቱ ተቀዳሚ አድርጎ ሊሰራቸው በያዛቸው እቅዶቹ ኃላፊነታቸውን በማያቋርጥ ሁኔታ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
አዲሱ ሊቀመንበር፤ በአፍሪካ ምድር ሰላም እና ብልፅግና እንዲሰፍን በተለይም ደግሞ አጀንዳ 2063 ተግባራዊ እንዲሆን በትጋት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ይህንን ኃላፊነት በብቃት እንደሚወጡ ቃል በመግባት፤ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መፈለግ በሚል መርህ በአህጉሪቱ ላሉ ግጭቶች መፍትሄ መፈለግ ደቡብ አፍሪካ በሊቀመንበርነት ቆይታዋ ትኩረት ሰጥታ የምታከናውን ይሆናል ብለዋል።
የህብረቱ አባል ሀገራትም ለዚህ ኃላፊነት ስኬት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ሊቀመንበሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ በተለይም የ2063 አጀንዳን ለማሳካት የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል አህጉሪቱ የሚያስፈልጋትን የኢኮኖሚ ብልፅግና ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
አባል አገራቱ በኢኮኖሚ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲተሳሰሩ የሚሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የአህጉሪቱን ቢዝነስ ማንቀሳቀስ፣ የንግድ ልውውጡን ማስተሳሰር፣ ሴቶችን በማብቃት ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥና የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፏቸውን በማጎልበት ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሴቶችን በማብቃት እና በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ በማድረግ እንዲሁም 50 በመቶ ሴቶች በተግባር ወደ ስልጣን እንዲመጡ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል። በአጠቃላይ ያለሴቶች ተሳትፎ እድገትና ዴሞክራሲ የማይታሰብ በመሆኑ መጪው ዘመን በተግባር ሴቶችን ያካተተ እንዲሆን የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
‹‹አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች አህጉር ናት፤ ነገር ግን በዛው ልክ መስራት የሚጠበቅባትን ስራ አላከናወነችም፡፡›› ያሉት የህብረቱ ሊቀመንበር፤ ጊዜው ህብረቱ ተቀዳሚ አድርጎ ሊሰራቸው ያሰባቸውን ተግባራት በጋራ በመሆን ማከናወንን እንደሚጠይቅ አመልክተዋል፡፡
‹‹የአህጉሪቱ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ የሚደረገው በራሳቸው በአፍሪካውያን ነው›› የሚለውን መርህ መሰረት በማድረግ የሚሰራ መሆኑን የጠቀሱት ስሪል ራማፎሳ፤ በተለይ በአፍሪካ በሚታዩ ግጭቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ያለው አሸባሪነት ለልማትም ሆነ ለሰላም እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው፤ አፍሪካውያን ለጋራ ጥቅም በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአህጉሪቱ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ግጭቶችን በመግታት ለአሸባሪዎች ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሊቢያ ላለው ችግር መፍትሄ ማፈላለግ የግድ መሆኑን አመልክተው፤ በደቡብ ሱዳን፣ በሱማሊያና በሌሎችም በአህጉሪቱ ያሉ የሰላም መታጣት ችግሮች በራሳቸው በአፍሪካውያን መፍትሄ አመንጪነት ሊወገዱ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፤ የ2020 የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ‹‹ግጭትን በማስቆም ለአፍሪካ ምቹ ሁኔታን መፍጠር›› የሚለው መሪ ሐሳብ ለሰላምና ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለልማት እና ለአህጉሪቱ ህዝቦች የኑሮ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጉዳዩ ላይ አፍሪካውያን ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በሰላም ማስፈንና በአሸባሪዎች ጉዳይ ላይ አፍሪካውያን በጋራ መስራት ያለባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ፤ አጀንዳው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2030 እና የአፍሪካ ህብረት በ2063 ያስቀመጡትን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ትልቅ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም አጀንዳው እንዲሳካ የተቻለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
‹‹አንድም የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማበት›› ማለት ከሰላምና ደህንነት ባሻገር፤ ዘላቂ ልማትና የሰብዓዊ መብት መከበርን የሚያካትት መሆኑን አመልክተው፤ ድህነት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የጥይት ድምጽ ችግሮች አሳሳቢ በመሆናቸው፤ አህጉሪቱ ለእነዚህ ሶስት ችግሮች ቅድሚያ ትኩረት ሰጥታ ልትሰራባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ የአንድ ዓመት ቆይታቸውን በማጠናቀቅ ስልጣናቸውን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው መርህ ምርጥ እንደነበር አስታውሰዋል። ግብፅም ህብረቱን ለአንድ ዓመት በመራችበት ወቅት ችግሮችን በመጋፈጥ መልካም ተፅዕኖ ለማሳረፍ መጣሯን አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት በተለይ ትኩረት ተደርጎ በሰላም ዙሪያ መሰራቱን ተናግረዋል። በቀጣይም በህብረት በመስራት አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ከአዲሱ የህብረቱ ሊቀመንበር ጎን እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል።
ትናንት በነበረው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በርካታ መሪዎች ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አህመድ አብዱላሂ፣ የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት የመሃሙድ አባስ ተወካይ እና ሌሎችም ይገኙበታል። መሪዎቹ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት በማግኘታቸው የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012
አስቴር ኤልያስ እና ሶሎሞን በየነ
ፎቶ፡- ሀዱሽ አብርሃ