– 96 ሺህ 250 ብር የሚገመት አደጋ
– 60 ሺህ ብር የሚገመት የኬብል ስርቆት ደርሶበታል
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትንስፖርት አገልግሎት ከሀምሌ እስከ ታህሳስ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በአምስት ባቡር ላይ በደረሰ የመኪና ግጭት እና በአጥር ላይ በደረሰ 36 አደጋ 96 ሺህ 250 ብር፤ እንዲሁም በኬብል ስርቆት ስልሳ ሺህ ብር የሚገመት ጉዳት እንዳጋጠመው አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የሴፍቲና ሴኩሪቲ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳምራዊት አወቀ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በማቋረጫዎች ላይ መኪና ከባቡር ጋር የመጋጨት አምስት አደጋዎች ተከስተዋል። በመሰረተ ልማት ላይ እና በአጥር ላይ ደግሞ 36 የመኪና አደጋ ተፈጥሯል። የደረሱት አደጋዎች በአማካይ 96 ሺህ 250 ብር ይገመታሉ። አብዛኛው የኬብል ስርቆት የሚፈፀመው በእስጢፋኖስ፤ በስታዲየምና በልደታ ጣቢያዎች አካባቢ ሲሆን፤ የተወሰደው ኬብል 60 ሺህ ብር የሚገመት ነው።
የሶስተኛ ወገን መድህን ያላቸው መኪናዎች የካሳ ክፍያ ይጠየቃል ያሉት ወይዘሮ ሳምራዊት፤ አብዛኛዎቹ አደጋዎች የቅርብ ጊዜ ስለሆኑ ግን የክፍያቸው ሁኔታ በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል። በኬብል ስርቆት ምክንያት ትራንስፖርቱ ወዲያው ባይስተጓጎልም በሂደት ችግር መፍጠሩ እንደማይቀር ግን ጠቅሰዋል። በውስጥ መስመር ላይ የተተከሉ ኬብሎችና የሲግናል ሲስተምን የሚያሳልጡ ኬብሎች ሲሰረቁ በባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ስርቆቶቹ በባለሙያ በሚመስል ደረጃ ተቆርጠው የሚወሰዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡
እንደ ወይዘሮ ሳምራዊት ገለፃ፤ በስርቆት የተያዙ ተጠርጣሪዎች በህግ ጥላ ስር ሆነው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል። ማህበረሰቡ ስርቆት ሲያይ በመጠቆም እንዲተባበር የጠየቁት ሀላፊዋ፤ በተለይ ኬብል ከተሰረቀ በኋላ ተረካቢ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012
መርድ ክፍሉ