የበዓላትን ሰሞን ያህል ባይሆንም ኤግዚቢሽን ማዕከል ደመቅ ብሏል። በተለይ ውጭው በመኪና ተጥለቅልቋል። ገሚሱ ጤፍ፣የዳቦ ዱቄት፣ቂቤና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ሲያስጭን፤ ሌላው ፍየል እና በግ እያሸከመ ወደ መኪናው ይወስዳል። ወደግቢ ሲዘልቁ በህብረት ስራ ማህበሩ ኤግዚቢሽን ላይ ፍየልና በግ በመኪና ከማቅረብ በተጨማሪ በአዳራሹ ውስጥ ቡና፣ ጤፍና የዳቦ ዱቄት ይዘው የቀረቡ ይበዛሉ።
ለጉብኝት የተገኘው ሰው ተዘዋውሮ ከመጠየቅ ይልቅ በቀጥታ ሰው ወደ በዛበት ያመራል። ምስር ክክና ድፍን ምስር፣ አተርና ባቄላ ጨምሮ የተለያዩ ጥራጥሬዎችን ያቀረበው የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማህበር ሸማቹ በዝቶለት አጠር ቀጠን ያለው ጠይም ወጣት ትንፋሽ እያጠረው እያለከለከ ምስር ክክ ይሰፍራል። አጠገቡ ያለው ጠይም ጎልማሳ አንድ ኪሎ ምስር 65 ብር እያለ ገንዘብ ይቀበላል። ፌስታልም ሆነ ለተከፈለው ክፍያ መልስ ሲጠየቅ “እንዳታስበሉኝ፤ እንዳታከስሩኝ” እያለ ይጮሃል። አቅራቢው የህብረት ሥራ ማህበር ነው ወይስ ግለሰቡ? ግራ ያጋባል።
ከባዛሩ ተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ሸዋው የሊበን የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን አንዱ ነው። ዩኒየኑ ጤፍ፣ የቢራ ገብስ፣ በቆሎ እና የከብት መኖ ይዞ ቀርቧል። በ1997 ዓ.ም በ20 ሺህ 847 ብር የተመሰረተ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ታደለ ንጉሴ እንደሚገልጹት፤ አሁን 26 ሚሊዮን ብር ላይ ደርሷል። ዩኒየኑ ከማህበራት ግዢ ፈፅሞ ወደ አዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች ገበያ አፈላልጎ በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ዩኒየኑ 15 ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም፤ ከከብት እርባታ እና የሰብል እህልን ገዝቶ ከመሸጥ የዘለለ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አለማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ታደሰ፤ በቀጣይ በውጪ ገበያ ላይ ለመሳተፍ ማቀዳቸውን ይገልፃሉ።
“ዩኒየኑ በየዓመቱ ኦዲት ይደረጋል። የተገኘው ትርፍ ለማህበራት ይከፋፈላል። በተጨማሪ ዩኒየኑ ለማህበራቱ መጋዘን ይከራያል። ብድርም ያበድራል።” ካሉ በኋላ፤ እነርሱ በሞያም ሆነ በዋጋ ማህበራትን የሚደግፉ መሆኑን ያመለክታሉ። ወደ ኢንቨስትመንት ያልገቡበት ምክንያት አቅማቸውን ማህበራትን ማገልገል ላይ በማዋላቸው መሆኑን በመጠቆም፤ ማህበራትን ያቋቋሙ መንግስታዊ አካላት ለማህበራት ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል አለማድረጋቸው ዕድገታቸውን እንደገታው ያብራራሉ።
ማህበራት መሪዎቻቸውን በየሶስት ዓመቱ መምረጥ እና አንድ መሪ ወይም ኮሚቴ ከሁለት ጊዜ በላይ፤ ማለትም ከስድስት ዓመት በላይ መመረጥ ባይኖርበትም ብዙዎቹ ከ12 ዓመት እና ከ15 ዓመት በላይ የሚሰሩ እና ለግል ጥቅማቸው በማድላት የማህበራትን ዕድገት እየገደቡ መሆኑን ይናገራሉ። ትርፉን ተቀብለው ለማህበሩ አባላት ከማከፋፈል ይልቅ ለግል ጉዳያቸው የሚያውሉት መሆኑንም ይጠቁማሉ።
ዩኒየኑ የህብረት ሥራ ማህበራት አባላት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ወደህብረተሰቡ በመውረድ ማህበሩ ከዩኒየኑ ያገኘውን ገንዘብ በመጠቆም ጥያቄ እንዲያቀርቡ የመገፋፋት ሥራ በመስራት ላይ መሆናቸውን በመጠቆም፤ የህብረተሰቡን ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የኦዲት ግኝቱን ማቅረብ ከህብረት ሥራ ማህበሩም ሆነ ከዩኒየኑ የተገኘውን በማሳወቅ ትክክለኛውን አካሄድ የመከተል ክፍተት መኖሩንም ነው ያመለከቱት፤ “ማህበሩ በሰራው ሥራ የተገኘው ትርፍ የአባላቱን ህይወት ከመቀየር ይልቅ በቀጥታ በኮሚቴዎች ኪስ ውስጥ ይገባል” የሚሉት አቶ ታደለ፤ ብዙዎቹ የህብረት ሥራ ማህበራት “ትርፍ አግኝተናል” ይላሉ። ነገር ግን፤ ትርፉን አያከፋፍሉም በማለት ነው ተናግረዋል።
የባዛሩ ተሳታፊና የድሬዳዋ ቀበሌ 05 ሸማቾች ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበር ተወካይ አቶ ሲሳይ ፈለቀ፤ ማህበሩ በ2000 ዓ.ም፤ በ394 አባላት፤ በ24 ሺህ 285 ብር ካፒታል የተመሰረተ መሆኑን ይናገራሉ። አሁን አንድ ሺህ 919 አባላት ያሏቸው ሲሆን፤ ሁለት ሚሊዮን 542 ሺህ ብር ያላቸው መሆኑን ያመለክታሉ። የቁጥጥር ኮሚቴ፣ የሥራ አስፈፃሚ፣ የሽያጭ እና የገበያ ትስስር ክፍል፣ የመጋዘን፤ የጥበቃ ሰራተኞችን ጨምሮ በሞያ ታግዞ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ያብራራሉ። በተከታታይ በጥንቃቄ ማህበሩ ኦዲት እየተደረገ መሆኑን እና ለአባሎቻቸው የትርፍ ክፍፍል እንደሚያደርጉ በመጠቆም፤ነገር ግን ዕድገታቸውና ወደ ኢንቨስትመንት የማምራት ሁኔታ ላይ ክፍተት መኖሩን ያምናሉ።
በቅድሚያ በአፍሪካ ገበያ ላይ ለመሳተፍ፤ በመቀጠል ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ገበያ የመሳተፍ ዕቅድ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ ነገር ግን ራሳቸውን ለማሳደግ ዳቦ ቤት ለመክፈት ቢያቅዱም የቦታ ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸው ይገልፃሉ።
በዚህ ረገድ፤ ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ዘወትር ከመውቀስ ይልቅ መንግስትና ህብረተሰቡ በተለይም መገናኛ ብዙሃን ቢያግዟቸው በተሻለ መልኩ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
ሊቻ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ያመረተውን ዱቄት ይዛ የቀረበችው ወጣት ብርቅነሽ ደምሴ እንደገለፀችው፤ ዩኒየኑ 19 ዓመታት እንዳስቆጠረ እና ፋብሪካ ገንብተው ከዳቦ ዱቄት ባሻገር መኖና ማዳበሪያ ማምረት ጀምረዋል። ናዝሬትና ሆሳዕና ምርታቸውን በማቅረብ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ዩኒየኑ በ19 ዓመታት ቆይታው በደንብ ያላደገበት ምክንያት የዳቦ ዱቄቱን ለማዘጋጀት ከአርሶ አደርና ከማህበራት ስንዴ ሲገዙ አርሶ አደሩን ለመጥቀም ከነጋዴ በላይ ገንዘብ አውጥተው ገዝተው ያመረቱትን ደግሞ ነጋዴው ከሚሸጥበት ገንዘብ በታች በመሸጣቸው ትርፋቸው ብዙ ባለመሆኑ ዕድገታቸው ውስን መሆኑን ያመለክታሉ።
የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር፤ ህብረት ሥራ ማህበራት እንደስራ (እንደቢዝነስ) አስቦ የመንቀሳቀስ፤ በኢንቨስትመንት ላይ የመሳተፍ ክፍተት አለባቸው። በእውቀት የመመራት፤ በሞያ የመተጋገዝ ችግር የሚስተዋልባቸው ሲሆን፤ ይህን ችግር ለማቃለል ኤጀንሲው በተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል። በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጥ እየተስተዋለ ነው። ከዚህ ዓመት በኋላ ማህበራቱ አንድ ደረጃ ከፍ ይላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012
ምህረት ሞገስ